ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ በኢራን ወደ 100 የሚጠጉ ስታርሊንኮች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል አሉ
የቢሊየሩ በኢራን አገልግሎት የመጀመር ጥረት በአማሪካ እንደሚደገፍ መረጃዎች ያመለክታሉ
የብሮድባንድ አገልግሎቱ ኢራናውያን "የኢንተርኔት ነጻነትን እና የመረጃ ፍሰትን እንዲኖራቸው" የሚያስችል ነው ተብሏል
የዓለማችን ባለጸጋውና የጠፈር ፍለጋ ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን (ስፔስ አክስ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤሎን መስክ ከሶስት ወራት በፊት ኩባኒያቸው በኢራን ውስጥ የሳተላይት የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚጀምር ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
መስክ በወቅቱ ስለእቅዳቸው ሲናገሩም በተቃውሞ እየታመሰች ባለችው ሀገር መሰል አገልግሎት መጀመሩ ኢራናውያንን "የኢንተርኔት ነጻነትን እና የመረጃ ፍሰትን እንዲኖራቸው" ያስችላልም ብለው ነበር፡፡
እናም ኩባኒያው አሁን ላይ በኢራን ውስጥ በርካታ “ኮከብ ማገናኛዎች” ወይም ስታርሊንኮች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
“በኢራን ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉ ኮከብ ማገናኛዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው”ም ብለዋል ኤሎን መስክ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት መረጃ፡፡
በሳተላይት ላይ የተመሰረተው የብሮድባንድ አገልግሎት ኢራናውያን በሀገሪቱ ዙሪያ እየተደረጉ ባሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ወቅት መንግስት ኢንተርኔትን እና አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ፕላንተፎርሞችን በመጠቀም በመንግስት የተጣለውን እገዳ አልፈው መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
የቢሊየነሩ መስክ በኢራን ውስጥ ኮከብ ማገናኛዎች ወይም ስታር ሊንኮች የመጀመር ጥረት በኢራን ህዝባዊ ተቃውሞ እጇ እንዳለ በሚነገርላት አሜሪካም ጭምር የሚታገዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች ከሶስት ቀናት በኋላ በእስር ላይ እያለች ህይወቷ ማለፉ የሚታወስ ነው።
የማህሳ አሚኒ ሞት ታዲያ በኢራን ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ማዕበል ቀስቅሷል።
በኢራን ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ተደረገው የሚታዩት አያቶላ አሊ ካሜኒ እንደዚህ አይነት ተቃውሞ ሲገጥማቸው በኢራን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መሆንም እየተገለጸ ይገኛል፡፡