ቢኒያም ግርማይ የቱር ደ ፍራንስ ውድድር አረንጓዴ ማሊያ ያሸነፈ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ
ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢኒያም የ3ኛ ፣ 8ኛ እና 12ተኛ ደረጃ ውድድሮችን በማሸነፍም አዲስ ታሪክ ጽፏል
“ቱር ደ ፍራንስ የአውሮፓውያን ብቻ ይመስለኝ ነበር” ያለው ቢኒያም ዘንድሮ በውድድሩ ነግሷል
ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢኒያም ግርማይ በቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ላይ ተወዳጁን “አረንጓዴ ማሊያ (Green Jersey) በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆኗል።
ባሳለፍነው ሰኔ 2016 የተጀመረው ታዋቂውና ተወዳጁ የቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር በዛሬው እለት ማለትም ሐምሌ 21 2016 ፍጸሜውን አግኝቷል።
በዘንድሮው ውድድር ላይ ከነገሱ ብስክሌተኞች መካከል የኢንተርማች ዋነቲ ቡድን አባል የሆነው የ24 ዓመቱ ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢኒያም ግርማይ አንዱ ነው።
ቢኒያም ግርማይ የቱር ደ ፍራንስ ውድድር አረንጓዴ ማሊያ (Green Jersey) ያሸነፈ የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን አዲስ ታሪክ ፅፏል።
ቢኒያም ግርማይ 387 ነጥብ በመሰብሰብ የአረንጓዴ ማሊያ አሸናፊነቱን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ጃስፐር ፊሊፖሴን አልፔሲን-ዴሴዩንክ በ354 ነጥብ እና የኮፊዲስ ብራያን ኮኳርድ በ208 ነጥብ ይከተሉታል።
ብስክሌተኛ ቢኒያም ግርማይ የቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር ውድድር የተለያዩ ደረጃዎች (Tour de France points classification) አሸናፊ ሆኖ በማጠናቀቅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን አዲስ መፃፍ ችሏል።
“ቱር ደ ፍራንስ የአውሮፓውያን ብቻ ይመስለኝ ነበር” ያለው ቢኒያም በማሸነፌ ደስተኛ ነኝ፤ በቃ የህይወቴ ምርጡ ቀን ነው “ ሲል ተደምጧል።
ቢኒያም ግርማይ በ2024 ቱር ደ ፍራንስ ውድድር የ3ኛ፣ 8ኛ እና 12ተኛ ደረጃ ውድድሮችን በማሸነፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ በመሆንም አዲስ ታሪክ በስሙ አስመዝግቧል።
በኤርትራዋ አስመራ ከተማ ተወልዶ ያደገው ቢኒያም ግርማይ በየዓመቱ የቱር ደ ፍራንስ ውድድሮችን በቴሌቪዥን ሲመለከት በሳይክል ውድድር ፍቅር እንደወደቀ ይናገራል።
“በዚህ ውድድር ላይ ብቸኛው ጥቁር ተወዳዳሪ ነኝ፤ ይህ ጥሩ አይደለም” ያለው ቢኒያም፤ በዚህ ውድድር ላይ በርካታ ጥቁር አፍሪካዊ ተወዳዳሪዎችን ማየት ምኞቴ ነው” ብሏል።
"ባለፈው አመት ባደረኩት የመጀመሪያ የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ተሳትፎ ልምድ አግኝቹ ሁሉንም ነገር በትክክል መምረት ችያለው ያለው ቢኒያም “ዛሬ ማሸነፌ የማይታመን ነው” ብሏል።