ዛሬ ያረፈው ኢትዮጵያዊው ድንቅ ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ ማን ነው?
ገረመው ደንቦባ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የሜልበርን ኦሎምፒክ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ማውለብለቡ ይታወሳል
በተለያዩ ውድድሮች የተሳተፈው ድንቅ ብስክሌተኛ 26 ዋንጫዎችና 32 ሜዳልያዎች ተሸልሟል
ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ ወክሎ ሰንደቋን ያውለበለበው ብስክሌተኛ ገረመው ደምቦባ ታህሳስ 7 ቀን 1925 ዓ.ም በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ አካባቢ ተወልዷል።
የመጀመሪያ ደርጃ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ኮከበ ጽብሀ) ትምህረት ቤት የተማረው ገረመው፥ ገና የሰባት አመት ህጻን እያለ ብስክትሌት መንዳት መጀመሩን በአንድ ወቅት በተደረገለት ቃለምልልስ ተናግሯል።
ከሰፈራቸው ወደ ኮከበ ጽበሃ ትምህርት ቤት ለመሄድ ያለውን ርቀት እና የብስክሌት ፍቅሩን የተረዱት እናቱ በ30 ብር የገዙለት አዲስ ብስክሌትም እስከ ሜልቦርን ለዘለቀው የስፖርት ህይወቱ ትልቅ ጅማሮ ሆነች።
ወደ ትምህርት ቤት ጓደኞቹን አፈናጦ ብስክሌት መንዳትን የእለት ተዕለት ተግባሩ ያደረገው የያኔው ታዳጊ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1943 ዓ.ም በብስክሌት ውድድር ቀርቧል።
በዚህም ረጅም ልምድ ካካበቱ የጣሊያንና ግሪክ ተወዳዳሪዎች ጋር ተፋልሞ ሰባተኛ ደረጃን መያዙ ገረመውን ለትልቅ ስኬት መንደርደሪያ እርሾ ሆነለት።
ገረመው ደንቦባ በ18 አመቱ ሰባተኛ ሆኖ ካጠናቀቀ በኋላ የብስክሌት ውድድሮች በአዲስ አበባ በስፋት ይካሄዱና ሰፊ ተመልካችንም ያገኙ ጀመር።
በ1945 ዓ.ም በተካሄደ ውድድርም የመጀመሪያውን ድሉን ያጣጣመው ገረመው ደንቦባ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ድልን በድል ላይ እየደረበ አለም አቀፍ መድረኮችን ይጠባበቅ እንደነበርም ነው ባደረጋቸው ቃለመጠይቆች ያወሳል።
የሜልቦርን የሰባት ቀን ታሪካዊ ጉዞ
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈችው በፈረንጆቹ 1956 በአውስትራሊያዋ ሜልበርን እንደነበር ይታወሳል።
የልዑካን ቡድኑ ሜልቦርን ለመድረስ ሰባት ቀን እና ሌሊት አውሮፕላን ላይ ማሳለፍ ግድ ብሎታል።
በውቅቱ የነበረውን ትዝታ ገረመው ለቪኦኤ ሲያስታውስ፥ "አሜሪካ ስሪት አሮጌ ዳኮታ የሚባል አውሮፕላን ተፈቀደልን፤ አውስትራሊያ ለመድረስ ሰባት ቀን ሰባት ለሊት ፈጀ፤ ሰባት ቀን አየር ላይ ስንቆይ ምግብ የለ ደርቀን ሥጋ እና አጥንታችን ተጣብቆ ከጦር ምርኮኝነት የተለቀቅን ይመስል ነበር" ብሎ ነበር።
ኢትዮጵያ በሜልቦርን ኦሎምፒክ በአስር የውድድር አይነቶች በአስራ ሁለት አትሌቶች ተካፍላለች።
ገረመው ደንቦባም በጎዳና ላይ በተደረገ የሳይክል ግልቢያ ውድድር ተሳትፎ 24ኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱ ይታወሳል። ይህ ውጤትም ከአፍሪካ እና ከእስያ ተፎካካሪዎቻቸው ቀዳሚ አድርጓቸዋል።
በውድድሩ ላይ ከገረመው በተጨማሪ መስፍን ተስፋዬ፣ ፀሐይ ባሕታ እና መንግስቱ ንጉሴ ተሳትፈዋል።
የገረመውና የቡድን አጋሮቻቸው ውጤትም በጊዜው ኢትዮጵያ በብስክሌት በቡድን አራተኛ እንድትወጣ ማስቻሉን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ከብስክሌተኝነት ወደ አሰልጣኝነት
ገረመው በጣሊያን ሮም 1960 በተካሄደው 17ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፏል።
ለድል የሚጠበቀው ብስክሌተኛ ግን ስፖርታዊ ጨዋነት በጎደላቸው ተወዳዳሪዎች መሃል ላይ ተጎዳ።
ፍጥነት ላይ ያለ የብስክሌቱን ጎማ ከኋላ ነክተው እንዲወድቅ አድርገውት ትከሻውና እግሩ ተሰበረ፤ በሄሊኮፕተርም ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ግድ ሆነ።
ይህ አሳዛኝ አደጋ ገረመውን ከሚወደው የብስክሌት ውድድር ሊያርቀው ቢያስገድድም ከስፖርት ሜዳ ግን አላጠፋውም፤ ፊቱን ወደ አሰልጣኝነት በማዞር በፈረንጆቹ በ1968 ጃፓን ባዘጋጀችው 19ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተካፈለውን ቡድን እየመራ ተጉዟል።
በ1973 በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው ሁለተኛ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የብስክሌት ቡድን ይዞ በመጓዝ ወርቅ ይዞ በመመለስም በተወዳዳሪነት ያስመዘገበውን ውጤት በአሰልጣኝነትም ደግሞታል።
ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ሁሉ ስኬታማ እንደሆነ የሚነገርለት ገረመው ደንቦባ፥ በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ 26 ዋንጫዎች እና 32 ሜዳልያዎች ተሸልሟል።