በኔዘርላንድ የሚኖሩ ኤርትራዊያን እርስ በርስ መደባደባቸው ተገለጸ
በኔዘርላዷ ሄግ የሚኖሩ ኤርትራዊያን እርስ በርስ ተደባድበው አራት ፖሊሶች ተጎድተዋል ተብሏል
ኤርትራዊያን ከዚህ በፊት በጀርመን እና ሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ ግጭት መግባታቸው አይዘነጋም
በኔዘርላንድ የሚኖሩ ኤርትራዊያን እርስ በርስ መደባደባቸው ተገለጸ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኤርትራዊያን ተደባደቡ የሚል ዜና እየተለመደ የመጣ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በኔዘርላንዷ ሄግ ከተማ የሚኖሩ ኤርትራዊያን እርስ በርስ መደባደባቸው ተገልጿል፡፡
እንደ ኔዘርላንድ ታየምስ ዘገባ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት ላይ በተዘጋጀ የኤርትራ ባህላዊ ዝግጅት ላይ እየታደሙ በነበሩ እና ይህን ዝግጅት እናስቆማለን በሚል ተቃዋሚዎች መካከል ግጭት ተከስቷል፡፡
ግጭቱ በኔዘርላንድ በሚኖሩ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ እና ደጋፊዎች መካከል እንደተካሄደ ፖሊስ አስታውቋል
ከባድ ድብደባ ተከስቶበታል የተባለውን ይህን ግጭት የሀገሪቱ ፖሊስ ከብዙ ጥረት በኋላ ያስቆመው ሲሆን አራት ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡
ፖሊስ አክሎም በዚህ ግጭት የተሳተፉ ያላቸውን በርካታ ኤርትራዊያንን እንዳሰረ የገለጸ ሲሆን ምርመራ እንደሚያደርግ እና እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል፡፡
ሶስት ፖሊሶች በእጃቸው እና ጥርሳቸው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባለ ሲሆን ግጭቱ ከባድ እና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነበርም ተብሏል፡፡
በጀርመን በሚኖሩ ኤርትራዊያን መካከል ግጭት መከሰቱ ተገለጸ
ሁለት የሀገሪቱ ፖሊስ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ አንድ የህዝብ አውቶቡስም ከኤርትራዊያኑ በተወረወረ እሳት ምክንያት እንደተቃጠሉ ሲገለጽ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራዎች ተደርገው ጥብቅ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተገልጿል፡፡
ሌሎች የሀገሪቱ ዜጎች እና ጎብኚዎችም በኤርትራዊያኑ ጸብ ምክንያት የተለያዩ ጉዳቶች አስተናግደዋል የተባለም ሲሆን የሄግ ከተማ ከንቲባ ጉዳዩ በፍጹም ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በጀርመን፣ ስዊድን እና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ኤርትራዊያን እርስ በርስ ተደባድበው በፖሊስ እና ሌሎች ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡