አቶ ቢኒያም ምሩፅ ይፍጠር የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በትናንትናው እለት ታህሳስ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ፌዴሬሽኑን ለ4 ዓመታት የሚመራውን የፕሬዚዳንት ምርጫ ማካሄዱን የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
በፌዴሬሽኑ በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር 4 ዕጩዎች የቀረቡ ሲሆን፥ የአንጋፋው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ልጅ የሆኑት አቶ ቢኒያም ምሩፅ በምርጫው አሸናፊ መሆን ችለዋል።
ይህንን ተከትሎም አቶ ቢኒያም ምሩፅ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለቀጣይ 4 አመታት ከስራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በፕሬዚዳንትነት የሚመሩ ይሆናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ_ፌዴሬሽን አዲሱ ፕሬዝዳንት አቶ ቢኒያም ምሩፅ ይፍጠር፥ ከቀድሞ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ከአቶ ብርሀኑ መኮንን ጋር የሰነድ ርክክብም አድርገዋል።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት “የአባቴን ኢትዮጵያዊ የሩጫ ታሪክ እኔ በአመራርነት እና በኃላፊነት እንድወጣው ሁላችሁም ከጎኔ እንድትሆኑ በአክብሮት እጠይቃለሁ” ብለዋል።
በቆይታቸው መልካም ተግባር በማከናወን በአትሌቲክሱ በአዲስ አበባ ከተማ ውጤታማ ስራ ለመስራት ከስራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በመሆን የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል።