የጃፓን የጦር መርከብ እና አውሮፕላኖችን በመካከለኛው ምስራቅ ቅኝት ሊያደርጉ ነው
ቶኪዮ የንግድ መርከቦቿን ከጥቃት ለመጠበቅ የጦር መርከብና የቅኝት አውሮፕላኖችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ልታሰማራ መሆኗን አስታውቃለች ።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ጃፓንን እዚህ ውሳኔ ላይ ንድትደርስ እንዳደረጋትም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
የሀገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ሀገሪቱ በየዓመቱ ከምትገዛው ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ውስጥ 90 በመቶውን የምታገኘው ከዚሁ ቀጣና መሆኑን ገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ካቢኔ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ሄሊኮፕተር ተሸካሚ የጦር መርከብ እና ፒ-3ሲ (P-3C) የተሰኙ ሦስት የቅኝት አውሮፕላኖች ወደ ቀጣናው ይሰማራሉ።
አካባቢው ስላለበት ሁኔታ እና ስለ ጃፓን የንግድ መርከቦች ደህንነት መረጃዎችን ለመሰብሰብና ከአደጋ ለመከላከል ይሰራል ነው የተባለው።
ድንገተኛ አደጋ ካጋጠመ በስፍራው የተሰማሩት የጃፓን የጦር መርከብና አውሮፕላኖች እርምጃ እንዲወስዱ በሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ልዩ ትዕዛዝ እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።
በኦማን ባህረ ሰላጤ፣ በሰሜናዊ የዓረቢያን ባህርና በኤደን ባህረሰላጤ ቅኝት ያደርጋሉ ተብሏል።
የጃፓን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዮሺሂዴ ሱጋ የመካከለኛው ምስራቅ ሰላምና መረጋጋት ጃፓንን ጨምሮ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላምና ብልፅግና ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ምንጭ፡- ሮይተርስ