የዘረፋ ውንብድና ወንጀል የፈፀሙት የፖሊስ አባላት በእስራት ተቀጡ
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አካባቢ መንግስት የሰጣቸውን መሳሪያ ተጠቅመው የውንብድና ወንጀል የፈፀሙት የፖሊስ አባለት በጽኑ እስራት ተቀጡ፡፡
የክሱ ዝርዝር እንደሚያስረዳው 1ኛ ተከሳሽ ኮን/ል ወንድሙ ሞሲሳ 2ኛ ተከሳሽ ኮን/ል ደረሰ ማርቆስ ሲሆኑ ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ጥቅምት 20 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡45 ዲኤች ገዳ የገበያ ማዕከል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ወንጀሉን የፈጸሙት፡፡
ፖሊሶቹ ካልተያዙት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን በመኪና በመታገዝ ለወንጀሉ መፈፀሚያ የሚሆን ክላሽ የጦር መሳሪያ እና ዱላ በመያዝ የግል ተበዳይ አሚር አሊ እና በወቅቱ ሱቅ ውስጥ የነበረውን ዳውድ አሊን አስቀድመው በያዙት ካቴና እንዳሰሩ የክሳቸው ዝርዝር ያሳያል፡፡
ከዚያም ግለሰቦቹን በመደብደብ የያዙትን መኪና ወደ ሱቁ በማስጠጋት ካቆሙ በኋላ ተ/ሀይማኖት ገ/መድን የተባለው ያልተያዘው ግብርአበራቸው ዶላር ይዣለሁ ትዘረዝራለህ በማለት ዳወድን እየጠየቀው እያለ ሱቅ ውስጥ በመግባት ተቀምጦ የነበረውን ሁለት መቶ ሺ ብር በመውሰድ በተዘጋጀው መኪና በመሄድ የግል ተበዳይንና አብሮት የነበረውን ጓደኛውን ከሱቁ አርቅው ጨለማ ቦታ ላይ በመውሰድ ፈተው ይለቋቸዋል፡፡
ከዚያም ዞረው እንዳይመለከቷቸው በማስጠንቀቅ ለቀዋቸው ብሩን ይዘው የተሰወሩ ሲሆን ፤በወቅቱ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ሲያዙ ሌሎች የተሰወሩ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት የከባድ ውንብድና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ በምርምራ መዝገቡ መሰረት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በመያዝ በማስረጃነት አቅርቧል::ተከሳሾች ማንነታቸው ተረጋግጦ ክሱ ተነቦላቸው እንዲረዱት ከተደረገ በኋላ የወንጅል ድርጊቱን አልፈፀምንም በማለት ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችን ቃል ለፍርሰድ ቤቱ አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሾችን በተከሰሱበት አንቀጽ ስር ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈፀሙት የፖሊስ አባል ሆነው መሆኑን እንደ ክስ ማክበጃ በመያዝ 1ኛ ተከሳሽ በ11 አመት ፣ 2ኛ ተከሳሽ በ10 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል ይላል የጠቅላይ አቃቤ ህግ መረጃ፡፡