አሜሪካ በምናባዊ ግብይት ተቋማት ላይ ምርመራ መጀመሯን ተከትሎ ነበር የክሪፕቶከረንሲ ዋጋ ያሽቆለቆለው
የዓለም ምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ምንዛሬ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።
ከሁለት ዓመት በፊት የምናባዊ ወይም ክሪፕዮከረንሲ ግብይቶች ተፈላጊነታቸው መጨመሩን ተከትሎ እስከ 60 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ደርሰው ነበር።
የምናባዊ ገንዘብ ተቀባይነት በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት እየጨመረ ቢመጣም እንደ ቻይና ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ግን እገዳ ጥለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለም በአሜሪካ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የምናባዊ ግብይት የጀመሩ ተቋማት ላይ ምርመራ መጀመሩ እና እንደ ሲልከን ቫሊ አይነት ባንኮች ኪሳራ ላይ መውደቃቸው የምናባዊ ግብይት ፍላጎት እያሽቆለቆለ ሊመጣ ችሏል።
በነዚህ ምክንያቶችም አንድ ቢትኮይን ከዚህ በፊት ከነበረበት 60 ሺህ ዶላር ወደ 10 ሺህ ዶላር እና በታች ለመመንዘር በቅቷል ተብሏል።
እንደ ሲኤን ኤን ዘገባ ደግሞ አሁን ላይ በርካታ የዓለም የቢዝነስ ድርጅቶች ምናባዊ ገንዘብ የመጠቀም ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ የምናባዊ ገንዘብ ምንዛሬ እንዲያድግ ማድረጉ ተገልጿል።
ለአብነትም አንድ ቢትኮይን ወደ 31 ሺህ 400 ዶላር በመመንዘር ላይ ደርሷል የተባለ ሲሆን ጭማሪው ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ትልቁ ነው ተብሏል።
ለዚህ ደግሞ እንደ ኮይን ቤዝ፣ ብላክ ሮክ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ተቋማት በምናባዊ ገንዘቦች ለመገበያየት በመፈለጋቸው እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ምናባዊ ግብይት ያልተፈቀደ እና ህገወጥ መሆኑን ጠቅሳ የዚህ ግብይት ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም አሰራሩ ስለሚዘረጋበት ሁኔታ በቀጣይ ዝግጅት እንደምታደርግ ከአንድ ዓመት በፊት ማሳወቋ ይታወሳል።