አሁን ላይ አንድ ቢቲኮይን በ27 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ይገኛል
በፈረንጆቹ 2009 ላይ ጃፓናዊው ሶታሺ ናካሞቶ እንደተፈጠረ የሚታመነው ቢቲኮይን የተሰኘው የድጅታል መገበያያ ገንዘብ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ይህ መገበያያ ገንዘብ ዋጋው በየጊዜው ከፍ እና ዝቅ ሲል የቆየ ሲሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ዋጋው ዝቅተኛ ምንዛሬን አስመዝግቦ ነበር።
ይሁንና በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት እያጋጠመ ባለው የዋጋ ግሽበት እና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት የቢትኮይን ዋጋ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉ ተገልጿል።
ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ60 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።
በተለይም በአሜሪካ የባንኮችን መክሰር ተከትሎ የቢትኮይን ፈላጊዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ዘገባዎች ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን በ27 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በመመንዘር ላይ ሲሆን የምንዛሬ መጠኑ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።
ቢትኮይን ያለ ማዕከላዊ ባንክ እና ሌሎች ተቆጣጣሪ ተቋማት እና ህጎች የማይመራ ሲሆን በርካታ ሀገራትም ዜጎቻቸው ቢትኮይን እና ሌሎች የድጅታል መገበያያ ገንዘቦችን እንዳይጠቀሙ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
ሕንድ፣ ቻይና፣ አሜሪካ እና ኢንዶኔዢያ ብዙ የቢትኮይን ድጅታል መገበያያ ገንዘብ ተጠቃሚ ዜጎች ያሉባቸው ሀገራት ናቸው።
ቢትኮይን በሚያዝያ ወር 2021 ላይ በታሪኩ ከፍተኛ ምንዛሬ መጠን ላይ የደረሰበት ወቅት ሲሆን በወቅቱ አንድ ቢትኮይን በ64 ሺህ ዶላር ተመንዝሮ ነበር።
የዓለማችን መገበያያ ገንዘብን እንደሚቆጣጠር የሚገለጸው ቢትኮይን ከ15 ዓመት በፊት ወደ ገበያ ሲቀላቀል የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከአንድ የዶላር ሳንቲም በታች ነበር።