ክሪፕቶ ከረንሲ፣ ቢትኮይን እና ሌሎች መሰል መገበያያዎች በኢትዮጵያ እንዳልተፈቀዱ ተገልጿል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው "ምናባዊ ንብረትን ወይም ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ" ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ የገንዘብ መደብ ብር እንደሆነና በብሔራዊ ባንክ በሌላ አኳኋን ካልተፈቀደ በስተቀር በሀገሪቱ የሚከናወኑ ማናቸውም የገንዘብ ግንኙነቶች ሁሉ የሚከፈሉት በብር እንደሚሆን የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 በግልጽ ይደነግጋል።
በተጨማሪም በክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 መሠረት በየትኛውም የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድም ሆነ ሥርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም ብሏል ተቋሙ በመግለጫው፡፡
ባንኩ ከጥናት ተረድቻለሁ እንዳለው በአሁኑ ወቅት ከህግ እውቅና ውጪ የክሪፕቶ ከረንሲ፣ እንደ ቢትኮይን እና የመሳሰሉት የዲጂታል መገበያያ ገንዘብ አገልግሎት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መጥቷል።
በተጨማሪም ይህ ተግባር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት እና በተለይ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ለማሸሽ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል ብሏል።
እየተስተዋለ ያለው የዲጂታል መገበያያ ገንዘብን ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን እንዲጠብቅ ያሳሰበው ተቋሙ ይህን ፈጽመው በሚገኙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡም ይህንን ህገወጥ ተግባር የሚሠሩ አካላትን ሲመለከት ለብሔራዊ ባንክ እና ለሚመለከታቸው ሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ባንኩ ጥሪ አቅርቧል፡፡