የቢትኮይን ዋጋ ከሶስት ወራት በኋላ ዳግም አሻቀበ
የቢትኮይን ዋጋ ያሻቀበው ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ የመመረጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው ከተባለ በኋላ ነው
አሁን ላይ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ69 ሺህ ዶላር አልፏል
የቢትኮይን ዋጋ ከሶስት ወራት በኋላ ዳግም አሻቀበ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ የመጣው የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ጉዳይ ዋጋቸው ከፍ እና ዝቅ ሲል ቆይቷል፡፡
በያዝነው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት መጀመሪያ ወራት ላይ የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ዋጋ በፍጥነት እየጨመረ ቢመጣም ላለፉት የተወሰኑ ወራት ደግሞ ዋጋቸው ዳግም አሽቆልቁሎ ነበር፡፡
ከነዚህ ምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች መካከል አንዱ የሆነው ቢትኮይን ከሰሞኑ ከነበረበት የዋጋ ማሽቆልቆል ወደ መጨመር ተሸጋግሯል፡፡
የቢትኮይን ዋጋ እየጨመረ የመጣው ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ዋነኛ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የማሸነፍ እድላቸው ጨምሯል ከተባለ በኋላ ነው፡፡
የምናባዊ መገበያያ ገንዘብ ደጋፊ መሆናቸውን የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ቢትኮይን እና መሰሎቹን የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች የሚደረጉ ግብይቶችን የስርዓታቸው አንድ አካል እንደሚያደርጉ ከዚህ በፊት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያ የቢትኮይን ግብይት ማካሄድ የሚያስችል መረጃ ማዕከል ግንባታ ስምምነት ተፈራረመች
ይህን ተከትሎ ከሰሞኑ በተደረገ የቅድመ ምርጫ ጥናት ሪፖርት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን የማሸነፍ እድላቸው ከፍተኛ ነው ከተባለ በኋላ የቢትኮይን ዋጋ ወደ 69 ሺህ 487 ዶላር ከፍ ብሏል፡፡
የቢትኮይን ዋጋ ጭማሪ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን የዶላር ዋጋ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለው አቅምም እንደጨመረ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተለይም የአሜሪካ ዶላር ከአውሮፓ ህብረቱ ዩሮ እና ከብሪታንያው ፓውንድ ጋር ያለበትን ብልጫ ማጥበብ የቻለ ሲሆን ከቻይናው ዩዋን ጋር ደግሞ ብልጫውን ማስፋት ችሏልም ተብሏል፡፡