አንድ ቢትኮይን በ80 ሺህ ዶላር መመንዘር ጀመረ
ዶናልድ ትራምፕ መመረጣቸውን ተከትሎ እንደ ቢትኮይን ያሉ የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ዋጋ እየጨመረ ይገኛል
ትራምፕ ስልጣን እንደያዙ የአሜሪካ የግብይት ልውውጥ ኮሚሽነርን ከስልጣን እንደሚያነሱ መናገራቸው ይታወሳል
አንድ ቢትኮይን በ80 ሺህ ዶላር መመንዘር ጀመረ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ ተከትሎ እንደ ቢትኮይን አይነት የምናባዊ መገበያያ ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ መገበያያዎች ዋጋ እየጨመረ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን በ80 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ሲሆን ሌላኛው በኢለን መስክ ይደገፋል የተባለው ዶጅኮይን የተሰኘው መገበያያ ገንዘብም ጭማሪ እንሳየ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የክሪፕቶከረንሲዎች ዋጋ በተያዘው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ ብቻ የ80 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ የ10 ሺህ ዶላር ጭማሪ አሳየ
ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት አሜሪካ የክሪፕቶ ከረንሲ ማዕከል እንድትሆን እንደሚፈልጉ እና ለመሰል ግብይቶች የግብር ቅናሽ እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የክሪፕቶከረንሲ ግብይቶች እንዲሰፉ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንደሚከተሉ አስታውቀዋል፡፡
የወቅቱ የአሜሪካ የግብይት እና ልውውጥ ኮሚሽነር የሆኑት ጋሪ ገንስለርን ከሃላፊነት እንደሚያነሱ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በ2021 በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሾሙት ጋሪ ገንስለር የክሪፕቶ ዋጋ እንዲቀንስ የተለያዩ ጣልቃ ገብነቶችን አድርገዋል በሚል በዶናልድ ትራምፕ ትችት ቀርቦባቸዋል፡፡
የቢትኮይን ዋጋ የተያዘው 2024 ዓመት ሳይጠናቀቅ ከ100 ሺህ ዶላር ሊያልፍ እንደሚችል የተለያዩ ግምቶች ተሰጥተዋል፡፡