47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተደርገው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ለክሪፕቶከረንሲ ግብይት የግብር ቅናሽ እንደሚያደርጉ መናገራቸው ይታወሳል
የአሜሪካ ዶላር እና ቢትኮይን ዋጋ ጭማሪ አሳየ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየተካሄደ ሲሆን የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸው ተረጋግጧል፡፡
ትራምፕ እስካሁን በተረጋገጡ የወኪል መራጮች ምርጫ አማካኝነት 278 በ224 ድምጽ እየመሩ የሚገኙ ሲሆን በቀጣዮቹ ሰዓታት ውስጥ የምርጫው አጠቃላይ ውጤት ይታወቃል፡፡
የዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ ተከትሎ ዶላር ከሌሎች ሀገራት መገበያያ ገንዘቦች ጋር ሲነጻጸር እስከ 2 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡
የአሜሪካ ዶላር በተለይም ከፓውንድ ስተርሊንግ፣ ዩሮ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተፎካካሪ መገበያያ ገንዘቦች ጋር ያለውን ልዩነት አጥብቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እንደ ቢትኮይን አይነት የምናባዊ መገበያያ ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ መገበያያዎች ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በ100 ሺህ ዶላር ሊመዘር እንደሚችል ተገለጸ
አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን በ74 ሺህ ዶላር መመንዘር የቻለ ሲሆን ይህ ጭማሪም ከዶናልድ ትራምፕ ማሸነፍ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢቢሲ በቢዝነስ አምዱ አስነብቧል፡፡
ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት አሜሪካ የክሪፕቶ ከረንሲ ማዕከል እንድትሆን እንደሚፈልጉ እና ለመሰል ግብይቶች የግብር ቅናሽ እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ዋነኛ ደጋፊ የሆኑት ኢለን መስክ የቢትኮይን ግብይት ደጋፊ ሲሆን ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የመንግስት ወጪ መቀነስ እና የግብር ቅናሽ ማሳየት ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን ጥር ወር ላይ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ከተመለሱ እና መንግስታቸውን ሲመሰርቱ ኢለን መስክም ሀላፊነት ሊሰጣቸው እንደሚችል ተገልጿል፡፡