ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት ያደረገችው ጥረት የማዕከሉ ዋና መቀመጫ እንድትሆን ማድረጉ ተገልጿል
ዓለም አቀፉ የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ማዕከል ዋና መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከፈተ።
የዓለም ጥቁር ህዝቦችን ታሪክ፣ ቅርስ እና ትምህርት ለመዘከር የተቋቋሙው ይህ ማዕከል ዋና መቀመጫውን በኢትዮጵያ ከፍቷል።
ማዕከሉ ዋና መቀመጫውን በአዲስ አበባ የከፈተው ከሌሎች ሀገራት ጋር አወዳድሮ መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር ከመሆኗ በተጨማሪ ጥቁር ህዝቦች ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ ያደረገችው አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ እንደገባ ተገልጿል።
በአፍሪካ ህብረት በተካሄደው ስነ ስርዓት የማዕከሉ መስራቾች፣ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀንን ጨምሮ ዲፕሎማቶች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ እና ሰብዓዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሴሱማ እንዳሉት የጥቁር ህዝቦች ለነጻነታቸው የከፈሉት መስዋዕትነት በወጉ አለመሰነዱን ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም ጥቁር ህዝቦች ለዓለም ያበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ እየተሰረዘ ነው፣ ይህ ማዕከልም መደራጀቱ በዓለም ላይ ላሉ ጥቁር ህዝቦች ሁሉ ይጠቅማል ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው "የጥቁር ህዝቦች የታሪክ ማዕከል ዋና መቀመጫውን በአዲስ አበባ ማድረጉ ታሪካችን እና አበርክቷችን በሚገባ እንዲጠና ያደርጋል" ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም ካላት ስምንት ቢሊዮን ጠቅላላ የህዝብ ብዛት ውስጥ 18 በመቶው ጥቁር ህዝብ እንደሆነ የተመድ 2022 ሪፖርት ያስረዳል።
ብራዚል ደግሞ ከአፍሪካ ውጪ ከፍተኛ ጥቁር ህዝቦች የሚኖሩባት ሀገር ተብላለች።
እንደ ፎርብስ 2023 መረጃ ከሆነ በዓለም ላይ ካሉ 3 ሺህ ቢሊየነሮች ውስጥ የጥቁር ቢሊየነሮች ቁጥር 14 ብቻ ናቸው።