የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
ማይክ ሃማር በሱዳን ጦርነት ዙሪያ ከነገ ጀምሮ በጂቡቲ በሚካሄደው የኢጋድ ጉባኤ ላይም ይሳተፋሉ ተብሏል
አሜሪካ በሱዳን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲካሄድ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጻለች
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃማር በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ቆይታቸው በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ ምክክር ያደርጋሉ ብሏል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚታዩ ግጭቶችም በንግግር እንዲቆሙ፤ በግጭቶች ንጹሃን ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ እና የሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱም ጥሪ እንደሚያቀርቡ ጠቁሟል።
- አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለው ውጥረት እንዲረግብ ጠየቀች
- በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
ማይክ ሃመር የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በሱዳን ጦርነት ዙሪያ ከነገ ጀምሮ በጂቡቲ በሚያካሂደው የመሪዎች ጉባኤ ላይም ይሳተፋሉ።
ዘጠነኛ ወሩን በቅርቡ የሚይዘው የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ጦርነት ያደረሰው ጉዳት ላይ የሚመክሩት የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች ተፋላሚዎቹን ለማቀራረብ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ይወያያሉ ተብሏል።
ኢጋድ የኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎችን ያካተተ የአራትዮስ የመሪዎች መፍትሄ አፈላላጊ ቡድን አዋቅሮ በሰኔ ወር በአዲስ አበባ የሱዳን ተፋላሚዎችን መጋበዙ ይታወሳል።
የሱዳን ጦር ተወካይም አዲስ አበባ ቢገኙም ለአርኤስኤፍ ወገንተኛ አስተያየት ሰጥተዋል ያሏቸውን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በመቃወም በስብሰባው ሳይሳተፉ መቅረታቸውም አይዘነጋም።
በቅርቡ በናይሮቢ ጉብኝት ያደረጉት አልቡርሃን ይህን ወቀሳ የሚያላላ ምክክር ማድረጋቸውንም ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል።
የጂቡቲው የኢጋድ ምክክር የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች በጂዳ እየጀመሩ የሚያቋርጡትን ድርድር መቋጫ እንዲያበጁለት ምክክር ይደረጋል ተብሏል።
ከ5 ሚልዮን በላይ ሱዳናውያንን ያፈናቀለውን ጦርነት የሚመሩትን አልቡርሃን እና ጀነራል ሞሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ለማቀራረብ ንግግሮች እንደሚደረጉም ተገልጿል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሃመርም በጂቡቲው ጉባኤ ተሳትፈው ወደ ኳታር በማምራት በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በሚመክረው የዶሃ ፎረም ይሳተፋሉ።
በአዲስ አበባም ከአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጋር በካርቱም ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለመፍጠር ውይይት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።