የምስራቅ አፍሪካው ማህበረሰብ የንግድ ጥምረት በትናንትናው እለት ሶማሊያን 8ኛ አባሉ አድርጎ ተቀብሏታል
ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካን የንግድ ማህበረሰብ ተቀላቀለች።
አዲስ እድሎችን እያማተረች ያለችው ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካውን የንግድ ማህበረሰብ ጥምረት ተቀላቅላለች።
የምስራቅ አፍሪካው ማህበረሰብ የንግድ ጥምረት በትናንትናው እለት ሶማሊያን 8ኛ አባሉ አድርጎ ማስገባቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሶማሊያ ወደ ጥምረቱ መቀላቀሏ በጦርነት የደቀቀው ኢኮኖሚዋ እንዲያንሰራራ እድል ይፈጥርላታል ተብሏል።
ብሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ታንዛንያ፣ ኡጋንዳን በአባልነት ያቀፈው የምራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ የንግድ ጥምረት የተቋቋመው በ2010 ነበር።
"ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብን ተቀላቅላለች፤ ለመሻሻል እና ለወዳጅነት በር ተከፍቷል" ሲሉ የሶማሊያ የኢንፎርሜሽን እና ባህል ሚኒስትር ዳውድ አዊስ በኤክስ ገጻቸው ገልጸዋል።
በምስራቅ አፍሪካ 3000 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ባለቤት የሆነችው ሶማሊያ የነዳጅ እና የጋዝ ክምችትም እንዳላት ይነገራል።
የሶማሊያ ከፍተኛ የመልማት አቅም ከጥምረቱ ሀገራት ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያስችላታል።
የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ በአስርት አመታት ውስጥ በኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች መሻሻል ቢያሳይም፣ ብልሹ አሰራሮች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ደካማ መሰረተልማቶች እና የንግድ ግጭቶችን ፈትነውታል።
17 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሶማሊያ ጥምረቱን ለመቀላቀል ለአመታት ጥረት ብታደርግም በሀገሪቱ ባለው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ምክንያት የተወሰኑ ሀገራት አባልነቷን ለመቀበል ፍላጎት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል ይላሉ ተንታኞች።
ከአል ቃኢዳ ግንኙነት ያለው አልሸባብ ሶማሊያ ከ2006 ጀምሮ እንዳትረጋጋ አድርጓታል።