ቦይንግ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራን የአፍሪካ ዳይሬክተር አድርጎ ሾመ
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ በአቪዬሽን ንግድ ዘርፍ ጥሩ ልምድ ያላቸው ሰው እንደሆኑ ተገልጿል
አምባሳደር ሔኖክ ከቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቁልፍ አመራሮች መካከል አንዱ ነበሩ
ቦይንግ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራን የአፍሪካ ዳይሬክተር አድርጎ ሾመ፡፡
የዓለማችን ስመ ገናናው የአቪዬሽን ተቋም ቦይንግ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራን የአፍሪካ ዳይሬክተር አድርጎ መሾሙን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ለዓልዐይን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በፈረንሳይ የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራን የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አድርጎ እንደሾመ አስታውቋል፡፡
ቦይንግ አምባሳደር ሔኖክን የሾመው ኩባንያው ከአፍሪካ ጋር የሚኖረውን የንግድ እና ሌሎች ግንኙነት እንዲያሳልጡለት መሆኑን ገልጿል፡፡
አምባሳደር ሔኖክ አዲስ አበባ ሆነው ስራቸውን ያከናውናሉ የተባለ ሲሆን በቦይንግ የመካከለኛው ምስራቅ፣ ቱርክ እና አፍሪካ ፕሬዝዳንት ለሆኑት ኩልጂት ጋታ አውራ ጋር ይሰራሉ ተብሏል፡፡
ቦይንግ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እንደሚከፍት የገለጸ ሲሆን አምባሳደር ሔኖክ ደግሞ የኩባንያውን የአፍሪካ ስራዎች እንደሚመሩ አስታውቋል፡፡
አምባሳደር ሔኖክ በአቪዬሽን ንግድ ዘርፍ እና መንግስታዊ ግንኙነቶችን በመምራት ጥሩ ልምድ እንዳለቸው የገለጸው ቦይንግ በአፍሪካ ያለውን ንግድ እንደሚሻሽሉለት አስታውቋል፡፡
አምባሳደር ሔኖክ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባልደረባ የነበሩ ሲሆን በተለይም የተቋሙን ስትራቴጂክ እቅድ በመምራት እና በምዕራብ አፍሪካ ላለው የአስካይ አየር መንገድን በቦርድ አመራርነት መርተዋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ 67 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ተስማማ
እንዲሁም ኢትዮጵያ በፈረንሳይ፣ ፖርቹጋል፣ ስፔን፣ ሞናኮ እና አካባቢው ባሉ ሀገራት የኢትዮጵያን ጥቅሞች ለማስከበር በአምባሳደርነት ለሶስት ዓመታት መስራታቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደር ሔኖክ ቦይንግን ከመቀላቀላቸው በፊት ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለገባው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ፡፡
በቦይንግ የመካከለኛው ምስራቅ፣ ቱርክ እና አፍሪካ ፕሬዝዳንት ለሆኑት ኩልጂት ጋታ አውራ በአምባሳደር ሔኖክ ሹመት በሰጡት አስተያየት “ ቦይንግ በአፍሪካ ከገባ 75 ዓመታት እንደሆነው እና አዲሱ የቦይንግ አፍሪካ ዳይሬክተርም የኩባንያውን ተሳትፎ እና ውጤታማነት ያሳድጉታል ብዬ አምናለሁ“ ብለዋል፡፡