አሜሪካ ለእስራኤል የ14 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ልታደርግ ነው
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ወደ ቴል አቪቭ ያቀናሉ
ብሊንከን ከእስራኤል አምባሳደሯን ያስወጣችውን ዮርዳኖስም ይጎበኛሉ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ወደ እስራኤል ያቀናሉ።
ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በሚያደርጉት ምክክር የዋሽንግተንን ድጋፍ በድጋሚ ያረጋግጣሉ ተብሏል።
በፍልስጤማውያን ንጹሃን ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንዲቀንስና የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ጦርነቱ ጋብ እንዲል ኔታንያሁን ያግባባሉ ብለዋል የብሊንከን ቃል አቀባይ።
ሚኒስትሩ በግብጽ እና ኳታር መሪነት እየተካሄደ ባለው በሃማስ የታገቱ ሰዎችን የማስለቀቅ ድርድር ዙሪያም ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል።
የአሜሪካው ዲፕሎማት ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን ካደሱ የአረብ ሀገራት አንዷ ወደሆነችው ዮርዳኖስም ያመራሉ ነው የተባለው።
አማን እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ድብደባ በመቃወም በቴል አቪቭ የሚገኘውን አምባሳደሯን በትናንትናው እለት ማስወጣቷ ይታወሳል።
ጦርነቱ ካልቆመ የእስራኤል አምባሳደር ወደ አማን ድርሽ እንዳይል ማለቷም አይዘነጋም።
ብሊንከንም በዮርዳኖስ ቆይታቸው የቴል አቪቭና አማን ቅራኔን የሚያስታርቁ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚያደርጉ ነው የተገለጸው።
በጋዛ “የሰብአዊ ተኩስ አቁም” እንጂ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ግፊት ማድረግ ያልፈለገችው ዋሽንግተን በዛሬው እለት ለቴል አቪቭ የ14 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ታጸድቃለች ተብሎ ይጠበቃል።
ድጋፉ እስራኤል በየቀኑ በጋዛ ቦምብ እንድታዘንብ እንደመፍቀድ ይቆጠራል ያሉ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን እና እስራኤል እንዲሁም ለድንበር ጥበቃ የሚውል የ106 ቢሊየን ዶላር በጀት እንዲጸድቅላቸው መጠየቃቸው ይታወሳል።