እስራኤል ሁለት የሃማስ አዛዦችን መግደሏን አስታወቀች
ቴል አቪቭ በጅባሊያ የስደተኞች ጣቢያ ላይ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በጥቂቱ 195 ፍልስጤማውያን ህይወት ማለፉን ሃማስ ገልጿል
የመንግስታቱ ድርጅት የጃባሊያውን ጥቃት “የጦር ወንጀል” ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል
እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች ጣቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ195 በላይ መድረሱ ተነገረ።
ማክሰኞ እና ረቡዕ በተፈጸሙት ሁለት የአየር ድብደባዎች ከ120 በላይ ሰዎች የገቡበት አልታወቀም፤ 777 ሰዎች ደግሞ ቆስልዋል ብሏል ሃማስ።
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ፥ እስራኤል በስደተኞች ጣቢያው ላይ የፈጸመችው ጥቃት “በጦር ወንጀል” ሊያስጠይቅ የሚችል ነው ብሏል።
ቴል አቪቭ ግን በአየር ድብደባው ሁለት የሃማስ ወታደራዊ አዛዦችን መግደሏን እና የማዘዣ ጣቢያዎችን ማፈራረሷን ነው ያስታወቀችው።
“ሃማስ በንጹሃን መኖሪያ ህንጻዎች ውስጥ ሆን ብሎ ተደብቆ ጥቃት ለመፈጸም ጥረት ማደረጉን ቀጥሏል” በሚልም በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጥፋት ለማስተባበል ሞክራለች።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ፍልስጤማውያን ቁጥር 8 ሺህ 796 የደረሰ ሲሆን፥ ከሟቾቹ ውስጥ 3 ሺህ 648ቱ ህጻናት ናቸው።
እስራኤል በጀመረችው የምድር ውጊያ የተገደሉ ወታደሮች ቁጥር 17 መድረሱን ማሳወቋንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ከጋዛ ወደ ግብጽ
የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ሰዎች እና በጽኑ የቆሰሉ ፍልስጤማውያን በትናትናው እለት በራፋህ መተላለፊያ በኩል ወደ ግብጽ ማስገባት ተጀምሯል።
350 የአሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ አውስትራሊያ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና ዮርድኖስ ዜጎች እና 81 ፍልስጤማውያን የድንበር መተላለፊያውን አልፈው ግብጽ ገብተዋል።
በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥም 7 ሺህ 500 የውጭ ዜጎችን ከጋዛ ለማስወጣት ከስምምነት መደረሱ ነው የተነገረው።
እስራኤል፣ ግብጽ እና ሃማስ ከዚህ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ኳታር እና አሜሪካ የአደራዳሪነት ሚና ነበራቸው ተብሏል።