አንቶኒ ብሊንከን እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያንን የማያባራውን “የጥቃት አዙሪት እንዲያቆሙ” ጥሪ አቀረቡ
ብሊንከን ከፕሬዝዳነት ማሃሙድ ዐባስ እና የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ ጋር የተናጠል የስልክ ቆይታ አድርጓል
በቅርቡ ከጋዛ ወደ እስራኤል የተሰነዘረው የሮኬት ጥቃት አሜሪካ ታወግዛለችም ብለዋል ብሊንከን
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያንን የማያባራውን “የጥቃት አዙሪት እንዲያቆሙ” ጥሪ አቀረቡ፡፡
ብሊንከን ይህንን ያሉት በሁለቱም ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት ባለፉት ቀናት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ነው፡፡
በዚህም ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማሃሙድ ዐባስ እና የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ ጋር በተናጠል የስልክ ቆይታ ያደረጉት ብሊንከን “እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን በእስራኤል ዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ ያለውን የጥቃት አዙሪት እንዲያቆሙ እና ውጥረቱን ከሚያባብሱ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ አፅንዖት ሰጥተው ተናግሯል” ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ሁለቱም ወገኖች በ”አል-አቅሳ መስጊድ ግቢ” የሚፈጥሩትን ውዝግብና ግጭት እንዲያቆሙም ጠይቋል ብሊንከን፡፡
አል-አቅሳ መስጊድ ግቢ በፍልስጤማውያን ዘንዳ ሶስተኛው የእስልምና ቦታ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በተቃራኒው በአይሁዶች ዘንድ የመቅደስ ተራራና የአይሁድ እምነት ቅዱስ ስፍራ ተደርጎ የሚወሰድ በእየሩሳሌም ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው፡፡
ብሊንከን ከላፒድ ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ የአሜሪካ መንግስት ለእስራኤል ደህንነት “ጽኑ ቁርጠኝነት” እንዳለውና በቅርቡ ከጋዛ የተሰነዘረው የሮኬት ጥቃት እንደሚያወግዝ ገልጸውላቸዋል፡፡
እንደ ላፒድ ሁሉ ከዐባስ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት ብሊንከን፡ ሀገራቸው አሜሪካ የፍልስጤማውያንን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗ አረጋግጧል።
ነገር ግን ሁለቱም ሀገራት በመካከላቸው ላለው ውጥረት “መፍትሄ ይስጡ” ሲሉ አሳስቧል ብሊንከን፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትላንት ማምሻውን እንዳስታወቀው ከሆነ በስቴት ዲፓርትመንት የምስራቁ ዓለም ጉዳዮችን በጥልቀት እንደሚያውቁ የሚነገርላቸው ረዳት ጸሃፊ ዬል ሌምፐርት በቅርቡ ወደ ዮርዳኖስ፣ እስራኤል፣ ዌስት ባንክ እና ግብጽ በመጓዝ በቀጠናው ያለውን "ውጥረት መቀነስን" ያለመ ውይይት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
የረዳት ጸሃፊዋ ዬል ሌምፐርት ጉብኝት ለሚቀጥሉት ስድስት ቀናት ይቆያልም ነው የተባለው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ከፍልስጤም በተተኮሰውና በእየሩሳሌም ቅዱስ ስፍራ አካባቢ የደረሰውን የሮኬት ጥቃት ተከትሎ፤ እስራኤል ከረዥም ወራት በኋላ በጋዛ ሰርጥ ላይ የመጀመሪያውን የአየር ጥቃት አካሂዳለች፡፡
እስራኤል በወሰደችው የአጸፋጥቃት፤ 23 ፍልስጤማውያን እና አረብ-እስራኤላውያን መገደላቸውም ተሰምቷል፡፡ በዚም በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል ያለው ውጥረትና ሁከት እጅጉን እንደተባባሰ በመገለጽ ላይ ነው፡፡
የተፈጠረው ሁከት ከአይሁዶች የፋሲካ በዓል እና ከሙስሊሞች የተቀደሰ የረመዳን ወር ጋር በመገጣጠሙ ፤ ልክ እንደባለፈው አመት ከፍተኛ የሆነ ትርምስ እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡
ባለፈው አመት የተፈጠረውና 11 ቀናት የፈጀ ሁከት በጋዛ የተለያዩ አከባቢውች ከፍተኛ ውድመት ማስከተሉ አይዘነጋም፡፡