እስራኤል ዜጎቿን ለ4ኛ ዙር ልትከትብ ነው
የጤና ባለሙያዎች ግን ይህ ክትባት ሳይንሳዊ መሰረት የለውም በሚል በመተቸት ላይ ናቸው
4ኛ ዙር ክትባቱ ዝቅተኛ በሽታ የመከላከል አቅም ላላቸው ዜጎች የሚሰጥ ነው ተብሏል
እስራኤል ለዜጎቿ አራተኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ልትሰጥ ነው፡፡
ከ8 ሺህ በላይ ዜጎቿን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ያጣችው እስራኤል ቫይረሱን መከላከል የሚያስችል ክትባት በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡
ከዋና ክትባቶች በተጨማሪ ማጠናከሪያዎችን (ቡስተርስ) ለዜጎቿ የሰጠችው እስራኤል አሁን ላይ ደግሞ ሁለተኛውን የማጠናከሪያ ወይም አራተኛ ዙር ክትባት ልትሰጥ መሆኑን የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ናችማን አሽ ተናግረዋል፡፡
ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መዛመቱን ቀጥሏል
ይህ የማጠናከሪያ ክትባት በተለይም ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ እና ዝቅተኛ በሽታ የመከላከል አቅም ላላቸው ዜጎች እንደሚሰጥ ሚኒስትሩ አክልለዋል፡፡
ይሁንና የጤና ባለሙያዎች ግን 4ኛ ዙር ክትባቱን ለዜጎች መስጠት የሚያስችል እና ስለውጤታማነቱ እስካሁን የተጠና ጥናት የለም በሚል እቅዱን ውድቅ አድርገዋል፡፡
የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ግን የካንሰር ህሙማንን እና የሰውነት አካል ንቅለ ተከላ ያደረጉ ሰዎችን ጨምሮ ዝቅተኛ በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸው ዜጎች ክትባቱን ይወስዳሉ ሲል አስታውቋል፡፡
አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ የኮሮና ቫይረስ የሚጠፋበትን ጊዜ ተነበዩ
ክትባቱ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንት ውስጥ መሰጠት ይጀመራል ያለው ሚኒስቴሩ 4ኛው ዙር ክትባት በጥንቃቄ እና ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንደሚሰጥም አክሏል፡፡
እስራኤል የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ከአንድ ዓመት በፊት ከሌሎች አገራት ቀድማ የጀመረች ሲሆን የማጠናከሪያ ክትባትንም በመስጠት ከዓለማችን ቀዳሚ አገር ናት፡፡
በእስራኤል የኮሮና ቫይረስ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎችን ሲያጠቃ 8 ሺህ 244 ሰዎችን ደግሞ እንደገደለ ጀሩሳሌም ፖስት ዘግቧል፡፡