ምርጫ ቦርድ እስካሁን በ221 የምርጫ ክልሎች ውጤት ይፋ መሆኑን አስታወቀ
በምርጫ ክልል ደረጃ ውጤት ይፋ በማድረግ አማራ ክልል ዝቅተኛ ነው ብሏል ቦርዱ
ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን በ2 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በሰጡት መግለጫ እስካሁን ከ440 የምርጫ ክልሎች ውስጥ 221 የምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሶሊያና እንዳሉት ቆጠራ የጨረሱት ምርጫ ክልሎች ወደ ማእከል እያጓጓዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምርጫ ክልሉ ወደ ማእከል ከማጓጓዙ በፊት ከስሩ ካሉት ምርጫ ጣቢያዎች የመጣውን ውጤት ደምሮ መለጠፉን ለህዝብ ይፋ ያደረገበት መረጃ መቅረብ ይኖርበታል ብለዋል ሶሊያና፡፡
እስሁን ባለው ሂደት የምርጫ ክልል ውጤት በማሳወቅ ደረጃ ወደ ኋላ የቀረው ክልል አማራ ክልል መሆኑን የገለጹት አማካሪዋ በክልሉ ካሉት 125 የምርጫ ክልሎች በ40 ዎቹ ብቻ ውጤት መለጠፉን አስታውቀዋል፡፡
አማካሪዋ ከምርጫ ጣቢያ ወደ ምርጫ ክልል ውጤት ለማጓጓዝ የትራንስፖርት ችግር፣ቆጠራ ቶሎ አለመጨረስና ወደ ምርጫ ክልል ሲመጡ ትክክለኛ ፎርም አለመሙላትን በምክንያትነት አቅርበዋል፡፡
ሶሊየና በምርጫ ክልል ድጋሚ ቆጠራ ሲደረግ ጊዜ መውሰዱን ተናግረዋል፡፡
እንደሶሊያና ከሆነ ኦሮሚያ ክልል 125 በሚሆኑ የምርጫ ክልል ውጤት በማሳወቅ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከ23 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ10 የምርጫ ክልሎች ብቻ ውጤት መገለጹን ሶሊያና ገልጸዋል፡፡
የምርጫ ክልሎች እስከ ነገ ባለው ጊዜ መጨረስ እንደሚጠበቅባቸውና ቦርዱም አጠቃላይ ጊዜያዊ ውጤት በጊዜው ለማሳወቅ ይጠቅመዋል ብለዋል አማካሪዋ፡፡
ሶሊየና አጠቃላይ ውጤቱን በፍጥት ለማሳወቅ ቅሬታ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን በተጠናከረ መልኩ በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡