አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ምርጫ ክልሎች ያለው የድምጽ ቆጠራ ሂደት ገና አልተጠናቀቀም
ቦርዱ የተቆጠሩ ድምጾች ወደ ምርጫ ክልሎች መምጣት መጀመራቸውን ማስታወቁ የሚታወስ ነው
ይህን ተከትሎ የቆጠራ ውጤቱን ወደ ማዕከል የላከ አንድም ምርጫ ክልል የለም
የመራጮች ድምጽ ውጤት በየምርጫ ጣቢያውም ይፋ የሆኑ ቢሆንም ውጤቶቹ ወደ ምርጫ ክልሎች ተልከው ውጤት እና ሌሎች ሪፖርቶች ገና በመጠናከር ላይ መሆናቸውን ሰምተናል።
የምርጫ ውጤቶችም በአምስት ቀናት ውስጥ በየምርጫ ክልሎች ተደራጅተው የክልል ምርጫ ቦርድ ቢሮዎች አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መላክ እንዳለባቸው የምርጫ ህጉ ያስረዳል።
አል ዐይን አማርኛ የድምጽ ቆጠራው እንዴት እየሄደ ነው? ሲል የክልል ምርጫ ቢሮ አስተባባሪዎችን ጠይቋል።
ከጠየቃቸው ምርጫ ክልሎች ውስጥ የአዲስ አበባ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልል እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር ምርጫ ክልሎች ይገኙበታል፡፡
ምርጫ ክልሎቹ እስካሁን ድረስ የድምጽ ቆጠራው እንዳልተጠናቀቀ ለአል ዐይን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር፣ በአማራ ክልል፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር እስከዛሬ ድረስ በምርጫ ክልል ደረጃ የተጠናቀቀ የድምጽ ቆጠራ አለመኖሩን ገልጸዋል።
በድምጽ ቆጠራው ላይ እስካሁን ያጋጠመ ችግር እንደሌለም ነው የተናገሩት፡፡ ሆኖም በድሬዳዋ አንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ በምርጫ ጣቢያው ይፋ በተደረገው እና ወደ ምርጫ ክልሉ በተላከው የቆጠራ ውጤት መካከል የምርጫ ውጤት አለመናበብ ማጋጠሙ ተገልጿል።
አል ዐይን ቆጠራውን እስከመቼ አጠናቃችሁ ወደ ቦርዱ ትልካላችሁ? በሚል ላነሳላቸው ጥያቄም “እንደምንም እስከ ነገ አጠናቀን ሙሉ ሪፖርቱን የፊታችን ቅዳሜ እንልካለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል አስተባባሪዎቹ።
የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች በቆጠራው ወቅት አለመገኘትና ጥሎ መሄድ በቆጠራው ያጋጠሙን ችግሮች ናቸው ያሉት የደቡብ ምርጫ ክልሎች አስተባባሪ በበኩላቸው ቆጠራውን በአንድ ምርጫ ክልል አጠናቀናል ብለዋል፡፡
ቆጠራው በአፋር ክልል በሚገኙት 25 ምርጫ ክልሎች እየተካሄደ ይገኛል ያሉት የክልል ምርጫ አስተባባሪ ደግሞ በ15ቱ ምርጫ ክልሎች ያለው የቆጠራ ሂደት መጠናቀቁን ገልጸውልናል፡፡
የቆጠራ ሂደቱ በምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ ድምጽ በተሰጠ በማግስቱ ነው ቆጠራው ተጠናቆ ይፋ የሚሆነው፡፡
ይህ የተቆጠረ ድምጽም ታሽጎ በልዩ ጥንቃቄ እና ጥበቃ ወደ ምርጫ ክልሎች ይጓጓዛል፡፡
የተቆጠሩ ድምጾች ከምርጫ ጣቢያዎች ወደ ምርጫ ክልሎች መምጣት መጀመራቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የቆጠራ ውጤቶቹ ተጠናቀው ሲደርሱት በ10 ቀናት ውስጥ ምናልባትም ከዚያ ባነሱ ቀናት ውስጥ የመጨረሻውን ውጤት አሳውቃለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው።