ከቦርዱ ትዕዛዝ ውጪ በነገሌ ምርጫ ክልል ምርጫ መካሄዱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
በደሴ ከተማ ተገኙ የተባሉት የድምጽ ሳጥኖች እንደገና መታየትና መቆጠር አለባቸው በሚል ተለይተው (‘ኳራንታይን’) የተቀመጡ ሳጥኖች መሆናቸውንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል
ምርጫው በባለስልጣን ትዕዛዝ መካሄዱን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ምርጫ ክልል በ100 ምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ ምርጫ እንዳይካሄድ የጣለውን ክልከላ በመጣስ ምርጫ መካሄዱን የኢትዮጵያ በሄራው ምርጨ ቦርድ አስታወቀ።
ከቦርዱ እውቅና ውጭ በምርጫ ክልሉ ትልቅ ግድፈት መፈጸሙን ያስታወቁት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ግድፈቱ የታተመው የምርጫ ክልሉ ድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ በህግ መስረት የተመዘገበን የግል ተወዳዳሪ ዕጩን ያላካተተ መሆኑን ተከትሎ ያጋጠመ ነው ብለዋል፡፡
ግድፈቱን በመረዳት ቦርዱ የነገሌ ምርጫ ክልል በአሁኑ ዙር ምርጫ ማድረግ የለበትም በሚል ትእዛዝ ከላይ እስከታች ሰጥቶ ነበር፡፡
ሆኖም “ማነንቱ ያልተጠቀሰ የመንግስት ባለስልጣን አሊያም የምርጫ ቦርድ አመራር” መቀጠል አለበት በማለቱ ምክንያት ምርጫው ከ100 በላይ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲቀጥል ተደርጓል።
ተግባሩ ህገ ወጥ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ቦርዱ ጉዳዩን ለፌደራል ፖሊስ ሪፖርት እንዳደረገና ጥፋቱ የማን እንደሆነና ማን ተጠያቂ እንደሚደረግ በቀጣይ እንደሚለይ ተናግረዋል።
በዚህም በምርጫ ክልሉ 100 ምርጫ ጣቢያዎች የተደረገው ምርጫ ውጤቱ ህጋዊ እንደማይሆንም ነው የተናገሩት።
ወ/ሪት ብርቱካን አያይዘውም በደሴ ከተማ ተገኙ የተባሉት 10 የድምጽ መስጫ ሳጥኖች በትክክል ሳይቆጠሩ ቀርተው ተለይተው የተቀመጡ (‘ኳራንታይን’) ሳጥኖች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህ ሳይቆጠር የተላከ ድምጽ በምርጫ ክልል ደረጃ እንደገና መታየትና እንደገና መቆጠር ስላለበት ምርጫ ክልሉ ለጊዜው ‘ኳራንታይን’ አድርጎ ለብቻው አስቀምጦት ነበረ ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ብርቱካን ሚዴቅሳ “ያ የማይሆን ትርጉም ተሰጥቶት ሃሰተኛ መረጃ ሊሆን ችሏል” ብለዋል፡፡
ሰብሳቢዋ “እስካሁን የደረሱን እንዲህ ዓይነት መጠነኛ ነገር ግን ውጤቱ ላይ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ስህተቶች አነስተኛ ናቸው” ያሉም ሲሆን ብዙዎቹ “እንደገና በመቁጠር ቃለ ጉባዔ በመያዝ ይህ ሲደረግ ደግሞ የፓርቲዎች ታዛቢ በቦታው እንዲሆን በማድረግ” ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የተቀላቀለ ድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ተጠቅመው የተገኙ ጣቢያዎች ጉዳይ ከምርጫ ክልሉ አጠቃላይ ውጤትና ድምጽ ሰጪ ብዛት አንጻር ታይቶ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናልም ነው ወ/ሪት ብርቱካን ያሉት፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ በአዲስ አበባ ምርመራ ላይ ያሉ ሁለት ምርጫ ክልሎች የመጨረሻ ውጤት ከውጤት ቋት ውስጥ እንደማይገባና በድጋሚ በመቁጠርና ሰነዱን እንደገና በማየት ሊስተካከሉ የሚችል ጉዳዮች ካሉ ሊታይ እንደሚችልም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የመጀመሪያው ዙር ማለትም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ምን ያህል ሰዎች ተሳተፉ? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም በቀጣይ መራጮች ቁጥር ቦርዱ የተጠቃለለ ውጤት ሲመጣለት ያሳውቃል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።