አሜሪካዊው ፖለቲከኛ ቦብ ሜንድዝ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከግብጽ ጉቦ መቀበላቸው ተገለጸ
በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ሜንድዝ ኢትዮጵያ ተገዳ ወደ ስምምነት እንድትመጣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጫና እንዲፈጥር አድርገዋል ተብሏል
ፖለቲከኛው እና ባለቤቱ ላይ በተደረገ ምርመራ በመጨረሻም በበርካታ ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል
አሜሪካዊው ፖለቲከኛ ቦብ ሜንድዝ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከግብጽ ጉቦ መቀበላቸው ተገለጸ፡፡
ቦብ ሜንድዝ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
የዘር ሀረጋቸው ከኩባ የሚመዘዘው ሜንድዝ ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤትን ከመቀላቀላቸው በፊት የኒው ጀርሲዋን ዩኒየን ሲቲን በከንቲባነት አገልግለዋል፡፡
እኝህ ጉምቱ ፖለቲከኛ በፈረንጆቹ 2020 ላይ የወቅቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አድርገዋል ተብሏል፡፡
እንደ አሜሪካ ድምጽ ዘገባ ከሆነ ፖለቲከኛው ይህን ያደረጉት ከግብጽ ባለስልጣናት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ጉቦ ከተቀበሉ በኋላ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ውይይት በማድረግ ላይ የነበሩ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ ውይይት ወደ ዋሸንግተን እንዲመጣ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
በዋሸንግተን በተደረጉት ተከታታይ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ በጫና ወደ ስምምነት እንድትመጣ ግፊት ሲደረግ እንደነበር እና ኢትዮጵያ ስምምነቱን አልፈርምም በሚል አቋሟ መጽናቷን በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ አውጥቶም ነበር፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 13 የግንባታ ዓመታት ጉዞ
አሜሪካ ይህን ጫና በኢትዮጵያ ላይ እንድታደርስ እኝህ ፖለቲከኛ ቦብ ሜንድዝ ከግብጽ ጉቦ በመቀበል በሀገራቸው መንግስት ላይ ጫና አድርሰዋል በሚል በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ፖለቲከኛው እና ባለቤታቸው ናዲስ ሜንደዝ በሌሎች የሙስና ወንጀሎችም ጥፋተኛ እንደሆኑ ሲገለጽ የፊታችን ጥቅምት ወር ላይ ለፍርድ ውሳኔው ተቀጥረዋል፡፡
ምንም አይነት ወንጀል አልሰራሁም የሚሉት ቦብ ሜንደዝ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መባላቸውን ተከትሎ ራሳቸውን ከስልጣን እንዲያገሉ ጫና እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡