የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት 13ኛ ዓመት “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ዛሬ ማክሰኞ 13ኛ ዓመቱን ደፍኗል። የግድቡ መሠረት የተጀመረበት 13ኛ ዓመትም “በኅብረት ችለናል!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።
የግድቡ ግንባታ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነበር በይፋ የተጀመረው።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሰረት ድንጋዩን አኑረዋል።
ከዚያም ወዲህ ግድቡ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል። የነበሩበትን እንደመርግ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተሻግሮ አሁን ላይ ወደ ፍጻሜው እየተንደረደረ ይገኛል።
ኢትዮጵያውያን ራሳቸው መሃንዲስም የፋይናንስ ምንጭም ሆነው ይገነቡታል የተባለለት ግድቡ 5 ዓመታትን እንደሚፈጅ ነበር በወቅቱ የተገለጸው።
ሆኖም በግንባታው መጓተት በተለይም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በኃላፊነት ወስዷቸው በነበሩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች መጓተት ምክንያት በተያዘለት እቅድ መሰረት መጠናቀቅ ሳይችል ቀርቷል።
ለዚህም በግንባታ ፕሮጄክቱ የተስተዋሉ የአስተዳደር እና የብልሹ አሰራር እንከኖች በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የፕሮጄክቱን ዋና ስራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘውን ህይወት እስከመንጠቅ የደረሱ ሁነቶች አጋጥመው እንደነበርም ይታወሳል።
የመንግስት ለውጥ ከመጣ ከ2010 ዓ.ም ወዲህም በግድቡ የግንባታ ፕሮጄክት ተስተውለዋል የተባሉ ህጸጾች ተነቅሰውና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ተቋራጩን እስከመቀየር እንዲሁም የተርባይኖቹን ቁጥር ከ16 ወደ 13 እስከመቀነስ የደረሱ እርምጃዎች ተወስደው ግንባታው ቀጥሎ አሁን አጠቃላይ የግንባታ ስራው 95 በመቶ ደርሷል።
የግድቡ አጠቃላይ የሲቪል ስራው ግንባታ የደረሰበት ደረጃ 98 ነጥብ 9 በመቶ ተጠናቋል የተባለ ሲሆን የኤሌክትሮ መካኒካ ስራውም በመፋጠን ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዉብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው አጠቃላይ ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከ13 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።
የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ግድቡ ካሉት ተርባይኖች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ዩኒት 10 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
በነሃሴ ወር 2014 ላይ ደግሞ ዩኒት 9 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 540 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨም ይገኛል።
ግድቡ በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ2017 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ ተገንብቶ ኢትዮጵያውያንና ጎረቤቶቿን ማገልገል እንደሚጀምር የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ ከአሁን ቀደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ ፕሮጀክቱ በቀጣይ ተጠናቆ የሚጠበቅበትን 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል። ይህም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ ነው።
የፋይናንስ ምንጭ ሆነው ግድቡን እንደሚገነቡ የተነገረላቸው ኢትዮጵያውያንም ዐይነተ ብዙ የገንዘብና የዐይነት ድጋችን እያደረጉ ነው።እስካሁንም በአጠቃላይ ባለፉት 13 ዓመታት ከህዝቡ ድጋፍ 19.1 ቢሊዮን ብር በላይ ከህዝቡ ማሰባሰብ መቻሉ ተገልጿል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገውን ህዝባዊ ድጋፍ ለማስቀጠልም 13ኛ የግንባታ ዓመቱን ታሳቢ ባደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ እስከ 300 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ተነግሯል።