የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ሥራ በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2016 የህዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን ከፍተዋል
ኢትዮጵያ በ2016 የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ ተገልጿል
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ሥራ በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡፡
ላለፉት ሁለት የክረምት ወራት ተዘግቶ የነበረው የህዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ዛሬ በይፋ ስራ ጀምረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ንግግራቸው ያለፈው ዓመት ምን እንደሚመስል እና የተየዘው ዓመት የመንግስን የትኩረት አቅጣጫ አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ስራ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
“ያለፈው ዓመት የዓባይ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት እና ከ90 በመቶ በላይ ግንባታው መጠናቀቁን የሰማንበት ዓመት ነበር” ያሉት ፕሬዝዳንቷ በያዝነው ዓመት የግድቡ የሲቪል ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋ፡፡
ፕሬዝዳንቷ አክለውም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ከማመንጨት ባለፈ የቱሪዝምና የውሃ ሀብት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የሞራል ልዕልና መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቷ አክለውም መንግስት በተያዘው ዓመት የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ የስራ እድል ፈጠራ ፣ የምግብ ዋስትና እና መልካም አስተዳድር ልዩ ትኩረት የሚሰጥባቸው ዋና ዋና ስራዎች እንደሚሆኑም በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ገልጸዋል፡፡
ስለ ህዳሴው ግድብ የኮርቻ ግድብ ምን ያህል ያውቃሉ?
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ መታቀዱንም ፕሬዝዳንቷል አክለዋል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ከሀገር ውስጥ የስራ እድል ፈጠራ በተጨማሪ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎችን በህጋዊ መንገድ ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ የስራ እድል መፈጠሩ ትልቅ ስኬት እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ የሰላም ስምምነት መፈረሙ፣ ኢትዮጵያ የብራዚል፣ ሩሲያ፣ሕንድ ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት የሆነው ብሪክስን በአባልነት መቀላቀሏ በዓመቱ የተመዘገቡ ስኬቶች ናቸው ተብሏል፡፡