የቦይንግ ምርቶች ኬቭ የሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በፍጥነት እንድትረብሽ እንደሚያግዟት ታምኖባቸዋል
ለአሜሪካ አየር ሃይል ቦምቦችን በማቅረብ የሚታወቀው ቦይንግ ለዩክሬንም ምርቶቹን ለመላክ መዘጋጀቱ ተነግሯል።
የአሜሪካው ታዋቂ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ለኬቭ ለመላክ የተዘጋጀው አነስተኛ ስፋት ያላቸውና እስከ 160 ኪሎሜትር በመጓዝ ጥቃት የሚያደርሱ ቦምቦችን ነው።
ኩባንያው ቦምቦቹንና የሚወነጨፉባቸውን ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ለዩክሬን ማቅረብ እንደሚጀምር ፖለቲኮ መጽሄት አስነብቧል።
ቦይንግ በፍሎሪዳ እና በሜክሲኮ ባህረ ሰላጤ ምርቶቹን መሞከሩንም ነው የጠቀሰው።
ሬውተርስ በበኩሉ ቦይንግ ከተሽከርካሪ ላይ የሚወነጨፉትን ቦምቦች እና ማስወንጨፊያ ተሽከርካሪዎቹን ወደ ዩክሬን በአውሮፕላን ለማጓጓዝ ስለማቀዱ ነው ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው።
የቦይንግ የቦምብ ማስወንጨፊያ ሂርማስ ከተሰኘውና አሁን ዩክሬን እየተጠቀመችበት ካለው የአሜሪካ የሮኬት ማስወንጨፊያ ስርአት በተሻለ ሩሲያ ላይ ጥቃት ማድረስ ይችላል ነው የሚለው ዘገባው።
ዋጋቸው ርካሽ፣ አነስተኛ መጠን ያላቸውና በፍጥነት ወደ ጦር ግንባር መሰማራት የሚችሉት የቦይንግ ተወንጫፊ ቦምቦች የሩሲያን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት ለመረበሽ ያስችላሉ ተብሏል።
ቦይንግም ሆነ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) ወደ ኬቭ ይላካሉ ስለተባሉት አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ያሉት ነገር የለም።
ታዋቂው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ የመከላከያ፣ ስፔስ እና ደህንነት ዘርፍ አቋቁሞ ለአሜሪካ ብሎም ለተለያዩ ሀገራት የጦር መሳሪያዎችን እያመረተ ያቀርባል።
ኩባንያው በተለይም ለአሜሪካ አየር ሃይል በሚያቀርባቸው አነስተኛ ቦምቦችና ሚሳኤሎች የሚታወቅ ሲሆን፥ በ2021 ከፍተኛ የሽያጭ ውል የፈጸመ ሶስተኛው ግዙፍ ኩባንያ እንደነበርም ይታወሳል።