ቦይንግ በበኩሉ የባለስልጣኑን ትዕዛዝ እንደሚያከብር እና ከደንበኞቹ ጋር የደህንነት ውይይቶችን እንደሚያደርግ አስታውቋል
ቦይንግ ኩባንያ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን እንዳያመርት ታገደ።
የዓለማችን ቁጥር አንድ አቪዬሽን ኩባንያ የሆነው የአሜሪካው ቦይንግ 737 ማክስ የተሰኙ አውሮፕላኖችን እንዳያመርት እገዳ ተጥሎበታል።
በአሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጠን የተጣለው ይህ እገዳ ጊዚያዊ ነው የተባለ ሲሆን ኩባንያው ተጨማሪ የደህንነት ማረጋገጫ እርምጃዎችን እንዲወስድም ተጠይቋል።
በአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ላይ የተጣለው ጊዜያዊ እገዳ ንብረትነቱ የአላስካ እና ዩናይትድ አየር መንገዶች የሆኑ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ መስኮቱ መገንጠሉን ተከትሎ እንደሆነ ኤፒ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎም ቦይንግ ሰራሽ የሆኑ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ተደርጓል።
የአሜሪክ አቪዬሽን ባለስልጣን ሀላፊ ማይክ ዌታከር እንዳሉት የማክስ 737 አውሮፕላኖች ከዚህ በፊት የነበረባቸውን የደህንነት ችግር ተፈቷል በሚል ዳግም ወደ በረራ እንዲመለሱ አድርገን ነበር ብለዋል።
ይሁንና አሁን ደግሞ ሌላ የደህንነት ችግር በማጋጠሙ ምክንያት ማክስ 737 አውሮፕላኖች ምርት በጊዜያዊነት እንዲቆም ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ቦይንግ ኩባንያ ከሶስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ አየር መንገዶች ላይ አደጋ ካጋጠመ በኋላ ሁሉንም ማክስ አውሮፕላኖች በመላው ዓለም እንዳይበሩ እገዳ ጥሎ ነበር።
በአውሮፕላኖቹ ላይ በተሰራ የደህንነት ማሻሻያ ስራዎች ማክስ አውሮፕላኖች ዳግም ወደ በረራ ተመልሰዋል።
በቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ አደጋ ማጋጠሙን ተከትሎ የኩባንያው አክስዮን ዋጋ በግማሽ እንዲቀንስ አድርጎትም ነበር።
ይህን ተከትሎ ለዓመታት በአቪዬሽን ትርፍ ቀዳሚ የነበረው ቦይንግ ኩባንያ ባለፉት አምስት ዓመታት በተቀናቃኙ ኤርባስ እንዲበለጥ አድርጎታል።