ዩክሬን ለጦር መሳሪያ ግዥ ያወጣሁት 40 ሚሊየን ዶላር የውሃ ሽታ ሆኗል አለች
አምስት የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አመራሮች ከመሳሪያ አቅራቢው ጋር ተመሳጥረው የምዝበራ ሙከራ ማድረጋቸው እንደተደረሰበትም አስታውቃለች
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በሙስኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል
ዩክሬን አምስት የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አመራሮችን በሙስና ወንጀል መጠርጠሯን ገለጸች።
የዩክሬን ደህንነት አገልግሎት እንዳስታወቀው አመራሮቹ 40 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ የሀገር ሀብትን በመመዝበር ነው የተጠረጠሩት።
ወታደራዊ አመራሮቹ 100 ሺህ የሞርታር ተተኳሽ ለመግዛት በነሃሴ ወር 2022 ስምምነት መፈራረማቸው ተጠቅሷል።
ለጦር መሳሪያው ግዥ የሚውለው ክፍያ (40 ሚሊየን ዶላር) አስቀድሞ ቢከፈልም አንድም ተተኳሽ ወደ ኬቭ አለመድረሱም ነው የተገለጸው።
የዩክሬን ደህንነት አገልግሎት ባደረኩት ምርመራ “አምስቱ ወታደራዊ አመራሮች ሊቪቭ አርሰናል ከተባለው መሳሪያ አቅራቢ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር የሀገሪቱን ሀብት መዝብረዋል” ብሏል።
አንደኛው ተጠርጣሪም ከዩክሬን ለመውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ስር መዋሉ የተነገረ ሲሆን፥ በግለሰቦቹ የተመዘበረው ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ይደረጋል ተብሏል።
ዩክሬን የአውሮፓ ህብረትን ለመቀላቀል በምትደርገው ጥረት ውስጥ ማነቆ የሆነባት የሙስና ጉዳይ በመከላከያ ሚኒስቴሯ በኩልም በስፋት ይታያል።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም በ2019 ወደ ስልጣን ሲመጡ ዋነኛ ትኩረታቸው ሙስናን መዋጋት እንደሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ባለፈው አመትም በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ከመሳሪያ ግዥ ጋር በተገናኘ በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ማባረራቸው አይዘነጋም።
በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የ2022 የሀገራት የሙስና እሳቤ ደረጃ ዩክሬን ከ180 ሀገራት ውስጥ 116ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ይሁን እንጂ ባለፉት አመታት እያከናወነቻቸው የሚገኙ የጸረሙስና ትግሎች በ10 አመት ውስጥ 28 ደረጃዎችን እንድታሻሽል ማድረጋቸውንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።