ቦኮሀራም በሰሜናዊ ምዕራብ ናይጀሪያ ኬቢ ግዛት ከ80 በላይ ተማሪዎችን አገተ
ቦኮሀራም የተሰኘው የጽንፈኞች ቡድን በሰሜናዊ ምዕራብ ናይጀሪያ ኬቢ ግዛት ከ80 በላይ ተማሪዎችን እንዳገተ ሮይርስ ዘግብል።
የሽብር ቡድኑ ከሶስት ሳምንት በፊት ተመሳሳይ የተማሪዎች እገታ የፈጸመ ሲሆን ድርጊቱን ተማሪዎቹን በመያዝ ከወላጆች ገንዘብ ለማግኘት እንደሆነ ዘገባው አክሏል።
ተማሪዎቹ በታገቱበት ትምህርት ቤት በመምህርነት እያገለገሉ የነበሩ ኡስማን አልዩ የተባሉ መምህር ለሮይተርስ እንዳሉት አጋቾቹ በትምህርት ቤቱ በር ላይ የነበረ አንድ ፖሊስን ከገደሉ በኋላ ከመማሪያ ክፍል ውስጥ ከ80 በላይ ተማሪዎችን ይዘው ሄደዋል።
የኬቢ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ እንዳሉት እገታውን የፈጸሙት የቦኮሀራም የሽብር ቡድን አባላት መሆናቸውን ገልጸው በእገታው ወቅት አንድ ፖሊስ ሲገደል አንድ ተማሪ ደግሞ ቆስሏል።
ይሁንን ቃል አቀባዩ ምን ያህል ተማሪዎች እንደታገቱ ከመናገር ተቆጥበው እገታ ፈጽመዋል በተባሉት ላይ እና ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ዘመቻ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ወላጆች እና የአካባቢው ነዋሪዎችም አጋቾቹ ተማሪዎቹ ሊደብቁባቸው ይችላሉ ባሏቸው ጫካዎች ውስጥ እየፈለጉ ነው ተብሏል።
በናይጀሪያ ካሳለፍነው ታህሳስ ጀምሮ ከ800 በላይ ተማሪዎች ከሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ታግተው የተወሰዱ ሲሆን ገሚሶቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ከፊሎቹ ደግሞ አስካሁን ያሉበት አይታወቅም።