የቦልሴናሮ ደጋፊዎች ሽንፈታቸውን ባለመቀበል አውራ ጎዳናዎችን በመዝጋት እንቅስቃሴን አስተጓጉለዋል
የምርጫውን ውጤት እንዳማይቀበሉ የገለጹት ቦልሴናሮ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
የብራዚል ፕሬዚዳንት ጃኢር ቦልሴናሮ በሳንምንቱ መገባደጃ እሁድ በተካሄደው ምርጫ ከተሸነፉ ወዲህ በመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ሽንፈታቸውን እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የምርጫ ውጤት ሙግትን እንደሚያቆሙ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል። ለፅ/ቤት ኃላፊያቸው የሽግግር ሂደቱን በተመራጩ ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዎ ሉላ ዳ ሲልቫ ተወካዮች ጋር እንዲጀመር ማዘዛቸውን ቦልሴናሮ አሳውቀዋል።
የቀኝ ዘመም ብሄርተኛ የሆኑት ቦልሴናሮ የስልጣን ዘመናቸውን የገታው ውጤት ከታወጀ በኋላ አስተያየት ለመስጠት ከ44 ሰዓታት በላይ ፈጅቶበታል ተብሏል። የቦልሴናሮ መዘግየት በምርጫው ውጤት ላይ ጥርጣሬ ለመጣል በማሰብ ነው የሚል ስጋትም አስነስቷል ሲል ሪዮተርስ ዘግቧል።
በዝምታቸው መሀል ደጋፊዎቻቸው ሽንፈታቸውን በመቃወም አውራ ጎዳናዎችን የዘጉ ሲሆን፤ ከፊሎቹም ተመራጭ ፕሬዚዳንት ሉላ ወደ ስልጣን እንዳይመለሱ ለማገድ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰልፈኞቹ አውራ ጎዳናዎችን በመዝጋት የነዳጅ ስርጭትን፣ የገበያ አቅርቦቶችን እንዲሁም ወደ ትላልቅ ወደቦች የሚላኩ እህሎችን አስተጓጉለዋል ነው የተባለው። ጃኢር ቦልሴናሮ አውራ ጎዳናዎችን የዘጉ ደጋፊዎቻቸው “የፍትህ መጓደል ስሜት” ያላቸው ናቸውም ብለዋቸዋል።
ቦልሶናሮ ለዜጎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ድምጽ የሰጧቸውን አመስግነው፤ በጥር ወር መጀመሪያ በሚደረገው የስልጣን ሽግግር ህገ-መንግስቱ የሚደነግገውን እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።