ብራዚል በ24 ሰዓት ውስጥ ከ4000 በላይ ዜጎቿን በኮሮና ቫይረስ አጣች
በአጠቃላይ በሀገሪቱ በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 337 ሺህ ደርሷል
በብራዚል 13ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
በብራዚል በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ4000 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ 19 ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ ተገለፀ።
በሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ሆስፒታሎችም በታማሚዎች እየተጨናነቁ መሆኑ ተነግሯል።
በበርካታ ከተሞች ታማሚዎች ህክምና በመጠባበቅ ላይ እያሉ ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን እና በሆስፒታሎች ላይ ካለው ከፍተኛ ጫና የተነሳ የሀገሪቱ የጤና ስርዓት አገልግሎት መስጠጥ ወደ ማቆም እየተቃረበ ነው ተብሏል።
በሀገሪቱ በትናትናው እለት በ24 ሰዓታት ብቻ 4 ሺህ 195 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በሀገሪቱ በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 337 ሺህ መድረሱን የብራዚል ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ይህም በሟቾች ቁጥር ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።
የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን በሀገሪቱ 13 ሚሊየን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል።
ቫይረሱ በሀገሪቱ በዚህ መጠን እየተስፋፋ ቢሆንም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃይር ቦልሶናሮ ግን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚወሰዱ የእንቅስቃሴ ገደብ እና ሌሌች እርጃመዎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ እንደከለከሉ ነው።
የእንቅስቃሴ ገደብ የኮሮና ቫይረስ ካስከተለው ጉዳት በበለጠ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ፤ የአንድ አንድ አካባቢ አስተዳደሮች የጣሏቸውን ክልከላዎችንም እንዲያነሱ እያደረጉ ነው ተብሏል።
በቤተ መንግስ አቅራቢያ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግርም፤ ሰዎችን ኳራንቲን ውስጥ ማስገባት ለድብርት እና ለከፍተኛ ሰውነት ውፍረት የዳርጋል ሲሉ መናገራቸውም ተሰምቷል።