የፕሬዝዳንት ፑቲንን አቅም አሳንሶ መመልከት እንደማይገባ ጆን ቦልተን ተናገሩ
የዋግነርን የሰሞኑ ሙከራ ተከትሎ የፕሬዝዳንት ፑቲን ስልጣን ላይ ጥያቄ የሚያነሱት ቢበዙም ቦልተን አይቀበሉትም
በፕሪጎዚን የሚመራው ዋግነር የሞከረው መፈንቅለ መንግሥት መክሸፉ ይታወሳል
የፕሬዝዳንት ፑቲንን እቅም አሳንሶ መመልከት እንደማይገባ የቀድሞው የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን ተናገሩ።
ባሳለፍነው አርብ ምሽት ጀምሮ የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪ የሆኑት ፕሪጎዚን ማመጻቸው ይታወሳል።
ፕሪጎዚን እና ጦራቸው የሩሲያ ጦር የአየር ላይ ጥቃት ከፍቶብናል በሚል የሀገሪቱን ወታደራዊ ጦር ማዘዣ ለመቆጣጠር ያለመ ጥቃት መክፈቱንም በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ይሁንና ቅዳሜ ዕለት የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሌኮሼንኮ ባደረጉት ድርድር ፕሪጎዚን የተመሰረተባቸው ክስ ተቋርጦ ወደ ጎረቤት ሀገር እንዲኮበልሉ ተፈቅዶላቸዋል።
ቀሪ የዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮችም ከሩሲያ መከላከያ ጋር አዲስ የስራ ስምምነት እንዲፈራረሙ ከስምምነት ላይም ተደርሶ ነበር።
ይህን ተከትሎ በርካታ የዓለማችን ሀገራት የዋግነር መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስልጣን እያበቃ ስለመሆኑ በትንቴኔያቸው በማስነበብ ላይ ናቸው።
የአሜሪካው ሲኤንኤን በተመድ የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር እንዲሁም የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የደህንነት አማካሪ የነበሩት ጆን ቦልተንን ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል።
እሳቸው በዋግነር በተፈጸመው እና በከሸፈው የመንቅለ መንግሥት ሙከራ ምክንያት የፕሬዝዳንት ፑቲንን አቅም ማሳነስ ስህተት ነው ብለዋል።
" ፕሬዝዳንት ፑቲንን አሳንሶ መመልከት ስህተት ነው፣ ማናችንም መረጃ የለንም፣ የዋግነርን ሙከራ መነሻ አድርገን ትንታኔ ላይ መድረስ አይቻልም"ሲሉም ቦልተን ተናግረዋል።
"በሞስኮ እየሆነ ያለው ነገር ያንን አያሳይም" ያሉት ጆን ቦልተን በዋግነር መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ምክንያት የዩክሬን መልሶ ማጥቃትም ስኬት ስለማስመዝገቡ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም ብለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ዋግነርን በማክሰም ላይ እንዳሉ የተገለጸላቸው ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዚህ በፊት ከዋግነር ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ትግበራ እንደሚቀጥል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ዋግነር በተለይም ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ያለው ሲሆን ከማሊ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ቡርኪናፋሶ እና ሌሎችም ሀገራት ጋር ያደረገው ስምምነት ይቀጥላል ተብሏል።