ፑቲን የዋግነር አመጽ የሀገር ክህደት ነው አሉ
ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው፥ ማንኛውም በሩሲያ መከላከያ ሃይል ላይ ጦር የሚያነሳ አካል የእጁን ያገኛል ሲሉ አስጠንቅቀዋል
ዋግነር ተዋጊዎቼ በሩሲያ ጦር የአየር ጥቃት ተገድለዋል በሚል በሩሲያ የጦር ጀነራሎች ላይ የአመጻ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዋግነር ቅጥረኛ ቡድንን በሀገር ክህደት ከሰሱ።
ፑቲን ከጥቂት ስአታት በፊት በቀጥታ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መክዕክት፥ ዋግነር የጦርነት አዋጅ ማወጁን ኮንነዋል።
ድርጊቱ የሀገር ክህደት ወንጀል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ የዋግነር ተዋጊዎች በሩሲያ መከላከያ ሃይል ላይ እንዳይተኩሱ አሳስበዋል።
“በሩሲያ መከላከያ ላይ ጦር የሚያነሳ የትኛውም አካል እርምጃ ይወሰድበታል” ሲሉም ነው በአስቸኳይ መግለጫቸው ያስጠነቀቁት።
ሩሲያን ለመጠበቅ የትኛውንም እርምጃ እወስዳለሁ ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፥ በሮስቶቭ ያለው ሁኔታ ለማረጋጋትም “ወሳኝ እርምጃ” ይወሰዳል ብለዋል።
ዋግነር ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ገብቶ በሮስቶቭ ከተማ የሚገኙ ወታደራዊ ማዘዣዎችን መቆጣጠሩን የቡድኑ መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን ትናንት ምሽት መናገሩ ይታወሳል።
በከተማዋ ታንኮቹን ማስገባቱንና የመንግስት ተቋማትን መክበቡን የሚያሳይ ምስልንም ለቋል።
ዛሬ ጠዋትም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ ፊት ለፊት መጥተው ካላናገሩን ወደ ሞስኮ እንዘልቃለን ሲል መዛቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
በዩክሬን ለወራት ተዋግቶ የባክሙት ከተማን ነጻ ያወጣው የዋግነር ቡድን፥ የሩሲያ መከላከያ ሃይል በቂ የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ ድጋፍ አላደረገልንም በሚል ሲከሰው ቆይቷል።
የሩሲያ መከላከያ ሃይል በበኩሉ ቡድኑ ይህን ወቀሳም ሆነ ትናንት ዋግነር ያቀረበው የተዋጊዎቼ ተገድለውብኛል ክስ ውድቅ አድርጎታል።
እልቂት ከመፈጠሩ በፊትም የዋግነር መሪው እጅ እንዲሰጥ እና ተዋጊዎቹም ከሩሲያ መከላከያ ሃይል ጋር ግጭት ውስጥ ከመግባት እንዲታቀቡ ጥሪ እየቀረበላቸው ነው።