የሩሲያ ጦርና የዋግነር ቡድን ግጭትን ተከትሎ ሀገራት ስለ ሁኔታው ምን አሉ?
ዋግነር ውጊያ ለማቆምና የቡድኑ መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን በቤላሩሰ እንዲቆዩ ትናነት ምሽት ተስማምቷል
አሜሪካ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ያለች ሲሆን፤ ዩክሬን ግጭቱ የሩሲያ ደካማነት ያሳየ ነው ብላለች
በሳለፍነው አርብ ምሽት የሩሲያው የቅጥረኛ ወታደር ቡድን ዋግነር ከዩክሬን ወደ ሩሲያ ገብቶ ሮስቶቭ የተሰኘችውን ከተማ አብዛኛው ክፍል መያዙን ተከትሎ በትናትናው እለት በሩሲያ ውጥረት ነግሶ ውሏል።
ዋግነር በመሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን በኩል የአመጽ ጥሪ ማስተላለፉን ተከትሎም በትናትናው እለት በሩሲያ ጦርና በዋግነር ቡድን መካከል ግጭቶች ተከትሰተው ነበር።
በሩሲያ የተከሰተውን ውጥረት ተከትሎም የተለያዩ የዓለማችን ሀገራት መሪዎች ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ጨምሮ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
ዩክሬን
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በትዊተር ገጻው ባሰፈሩት ጽሁፍ “የዋግነር ተግባር ሩሲያ ደካማ እንደነበረች ያሳየ ነው” ብለዋል።
"የሩሲያ ድክመት ግልጽ ነው፣ ሙሉ በሙሉ ደካማ ናት፣ ያሉት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ “ሩሲያ ወታደሮቿን እና ቅጥረኞቿን በምድራችን ላይ የምታቆይ ከሆነ የበለጠ ትርምስ፣ ሰቃይ እና ችግር ይገጥማታል” ሲሉ አስታውቀዋል።
"የክፉውን ሰይጣዊ መንገድ የሚመርጥ ሰው እራሱን ያጠፋል" ያት ዘሌንስኪ፤ “ለረዥም ጊዜ ሩሲያ ድክመቷን እና የመንግስቷን አረመኔነት ለመሸፈን ፕሮፓጋንዳ ስትጠቀም ነበር፤ አሁን ግን ማንም ውሸት ሊደብቀው የማይችለው ግርግር በዝቷል” ብለዋል።
አሜሪካ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሩሲያ ስላለው ሁኔታ ገለፃ እንደተደረገላቸው እናበሩሲያ ሊከሰቱ በሚችሉ ለውጦች ላይ ከአጋሮች ጋር እንደሚመክሩ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አዳም ሆጅ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው በሩሲያ ያለው ሁኔታ እያደገ አሊያም እያገረሸ ሲሄድ አሜሪካ አጋሮቿ ጋር በመሆን ሁኔታውን በቅርበት ትከታተላች ብለዋል።
ብሪታኒያ
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ "ሁሉም አካላት የሲቪል ዜጎችን የመጠበቅ ኃፊነት ሊሰማቸው ይገባል ሲሉ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል።
ሁኔታው በዚሁ እየቀጠለ ከሄደ ከአጋሮቻችን ጋር እየተገናኘን እንመክራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሁሉም በላይ አስፈላጊው ነገር ሁሉም ወገኖች የኃላፊነት መንፈስ እንዲያሳዩ ነው ”ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የአውሮፓ ህብረት
የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ሃላፊ ቻርለስ ሚሼል ህብረቱ “በሩሲያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ ነው” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። ከአውሮፓ መሪዎች እና ከቡድን7 አጋሮች ጋር በጉዳ ላይ ስለመነጋገራቸውም አስታውቀዋል።
"እየተካሄደ ያለው ጉዳይ በግልፅ የሩስያ የውስጥ ጉዳይ ነው" ያት ኃፊው "ለዩክሬን ያለን ድጋፍ" የማይናወጥ ነው" ሲሉ አስታውቀዋል።
ቱርክ
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ከሩሲያ አቻው ቨላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ የተወያዩ ሲሆን፤ ቱርክ ሩሲያ ውስጥ የታጠቀውን አመጽ "ሰላማዊ መፍትሄ" ለመፈለግ ዝግጁ ነች ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን እንደተናገሩት “እኛ እንደ ቱርክ በተቻለ ፍጥነት በሩሲያ ውስጥ ለተከሰቱት ክስተቶች ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ የበኩላችንን ለማድረግ ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ኢራን፣ ኳታር፣ ፓላንድ፣ ቤላሩስ እና ካዛኪስታንም በሩሲያ ስለተፈጠረው ሁኔታ መግከለጫ ከሰጡ ሀገራት መካል ይገኛሉ።
የሩሲያው ቅጠረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር በዩክሬን በሚገኙ ተዋጊዎቹ ላይ የሩሲያ ጦር የአየር ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ነበር ከሩሲያ ጦር ጋር ወደ ግጭት ያመራው።
የቡድኑ መሪ ፕሪጎዥን በድምጽ በተቀረጸ መልዕክቱ የሩሲያ ጦር መሪዎችን ለማስወገድ የትኛውንም እርምጃ እንወስዳለን ሲል መደመጡንም ሬውተርስ አስነብቧል።
በደቡባዊ ሩሲያ ሮስቶቭ የተጀመረው ከበባም እስከ ሞስኮ በመዝለቅ ወታደራዊ ተቋሙን እስከመቆጣጠር እንደሚደርስ ዝቷል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትናነት በቀጥታ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መክዕክት፥ ዋግነር የጦርነት አዋጅ ማወጁን ኮንነዋል።
ድርጊቱ የሀገር ክህደት ወንጀል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ “በሩሲያ መከላከያ ላይ ጦር የሚያነሳ የትኛውም አካል እርምጃ ይወሰድበታል” ሲሉም ነው በአስቸኳይ መግለጫቸው ያስጠነቀቁት።
ትናት ምሽት ላይ ዋግነር ውጊያ ለማቆም መስማማቱን የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሴንኮ መናገራውም ይታወሳል።
የፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፥ ቀኑን ሙሉ በተደረገው ምክክርም ፕሪጎዥን በሩሲያ ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ላለመግባትና የተጀመረውን ውጊያ ለማቆም መስማማቱን አስታውቋል።
የቅጥረኛ ወታደር ቡድኑ መሪ ተዋጊዎቹ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡንም መግለጫው ማመላከቱን አርቲ አስነብቧል።