ሩሲያ ከዩክሬን የተማረኩ ሊዮፓርድ ታንኮችን ወደ ትራክተርነት እንደምትቀይራቸው ገለጸች
ሞስኮ አውሮፓዊያን ለዩክሬን የሰጧቸውን ታንኮች እያወደመች መሆኗን አስታውቃለች
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ በስራ ላይ ያሉ ትራክተሮችን እንጂ ሊዮፓርድ ታንኮችን አለመምታቷን ገልጻለች
ሩሲያ ከዩክሬን የተማረኩ ሊዮፓርድ ታንኮችን ወደ ትራክተርነት እንደምትቀይራቸው ገለጸች፡፡
ለጥቂት ቀናት እና ለልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 16ኛ ወሩን ይዟል፡፡
ይህ ጦርነት አንዴ ሞቅ አንዴ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለ ሲሆን ዩክሬን ከአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ባገገኘችው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዋን በማካሄድ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ድል እየቀናት መሆኗን የገለጸችው ዩክሬን በሩሲያ ላይ ዋናውን ቡጢ ገና እንዳላሳረፈችም የገለጸች ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ የኪቭ መልሶ ማጥቃት ከወዲሁ መክሸፉን ገልጻለች፡፡
ዩክሬን ድል ትቀዳጅበታለች በሚል ከአሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት የሰበሰበችውን የጦር መሳሪያዎች እያወደመች መሆኑን የገለጸችው ሩሲያ በተለይም ሊዮፓርድ የተሰኘው የጦር ታንክ እየወደመ እና እየተማረከ መሆኑን ገልጻለች፡፡
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ ከሆነ ሩሲያ ለዩክሬን የተሰጡ የጦር ታንኮችን ወደ ትራክተርነት እንደምትቀይራቸው አስታውቃለች፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ ሊዮፓርድ ታንክን አወደምኩ በሚል የለቀቀቻቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች በግብርና ስራዎች ላይ የነበሩ ትራክተሮችን ስትመታ የሚያሳዩ ናቸው ስትል ውድቅ አድርጋለች፡፡
ዩክሬን በጀመረችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በርካታ መንደሮችን ከሩሲያ ጦር ነጻ ማድረጓን ገልጻ እየተገኘ ያለው ድል በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ በፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በኩል ገልጻለች፡፡