በህንድ የቦምብ ጥቃት ዛቻ በረራ አስተጓጉሏል
ከደልሂ ወደ ሙምባይ 186 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን በአህመዳድ ከተማ ለማረፍ መገደዱ ነው የተገለጸው
ሶስት የህንድ አየመንገዶች ባለፉት ሶስት ቀናት በደህንነት ስጋት ምክንያት ያለመዳረሻቸው አርፈዋል
በህንድ በአውሮፕላኖች ላይ የሽብር ጥቃት እናደርሳለን የሚሉ ዛቻዎች በረራዎችን እያስተጓጎሉ ነው።
በዛሬው እለት ከደልሂ ወደ ሙምባይ ሲጓዝ የነበረ የአክሳ ኤር ፍላይት አውሮፕላን አቅጣጫውን ወደ አህመዳድ ከተማ ለውጦ ለማረፍ መገደዱን የህንድ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ህጻናትን ጨምሮ 186 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን ከመንገደኛ የቦምብ ጥቃት ዛቻ እንደደረሰበት የአክሳ ኤር ቃል አቀባይ ለኢንዲያን ቱደይ ተናግረዋል።
አብራሪው ሁሉንም የደህንነት ፕሮቶኮሎች በማክበር በአህመዳድ ከተማ ሳርዳር ቫላባሃይ አለማቀፍ አውሮፕላን በሰላም ማሳረፍ መቻሉም ተገልጿል።
ሁሉም መንገደኞች ከአውሮፕላኑ እንዲወጡ መደረጉንም አየርመንገዱ ያስታወቀ ሲሆን፥ ስለቦምብ ጥቃት ዛቻው ግን ማብራሪያን አልሰጠም።
ባለፉት ሶስት ቀናት ሶስት የተለያዩ የህንድ አየመንገዶች አውሮፕላኖች በቦምብ ጥቃት ዛቻ ምክንያት ፈታኝ ጊዜን አሳልፈዋል።
በትናንትናው እለት 294 መንገደኞችን አሳፍሮ ከፓሪስ የተነሳው ቪስታራ የተሰኘው አየርመንገድ አውሮፕላን ወደመዳረሻው ሙምባይ ሲቃረብ ከመንገደኛ በእጅ የተጻፈ የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደርሶታል።
ከቫራናሲ ወደ ደልሂ ሊጓዝ የነበረ የኢንዲጎ አየርመንገድ አውሮፕላንም ተመሳሳይ ዛቻ ደርሶት የነበረ ቢሆንም ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጎ በደልሂ ኢንድራጋንዲ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፉ ተገልጿል።
ሶስቱም የቦምብ ጥቃት ዛቻዎች በረራዎችን ከማስተጓጎላቸው ውጭ አውሮፕላኖችን ያለመዳረሻቸው ሊያሳርፉና መንገደኞችን ሊያሸብሩ የሚችሉ እንዳልነበሩ ነው የተጠቆመው።
ይሁን እንጂ አየርመንገዶቹ ለመንገደኞቻቸው ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ተገቢውን እርምጃ መውሰዳቸው አስመስግኗቸዋል።