የትራምፕ እጩ የካቢኔ አባላት የቦምብ ጥቃት ዛቻ እየደረሰቸው ነው ተባለ
የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሆኑ የተመረጡትን ጨምሮ ቢያንስ ዘጠኝ እጩዎች በስልክ ጥሪ ቤታቸው በቦምብ እንደሚመታ ተነግሯቸዋል
ኤፍቢአይ እና ፖሊስ የተሿሚዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ጥበቃና ክትትላቸውን መቀጠላቸው ተገልጿል
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ የመረጧቸው እጩ የካቢኔ አባላት የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደረሰባቸው።
የአሜሪካ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) በቦምብ ጥቃት ኢላማው ውስጥ እነማን እንደገቡ ባይጠቅስም "በርካታ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ" መድረሱን ገልጿል።
እጩ የካቢኔ አባላቱ ቤት ላይ የቦምብ ጥቃት እንደሚፈጸም ሀሰተኛ የስልክ ጥሪዎች የተደረጉትም ፖሊስ ወደግለሰቦቹ ቤት በፍጥነት እንዲመጣ ለማድረግ በማለም ነው ብሏል።
ትራምፕ የመከላከያ፣ የቤቶች፣ የግብርና እና ሰራተኛ ሚኒስትር እንዲሆኑ የሾሟቸውን ጨምሮ በጥቂቱ ዘጠኝ ተመራጮች ላይ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያው መድረሱ ተገልጿል።
ፖሊስ ማክሰኞ እና ረቡዕ በእጩ የካቢኔ አባላቱ ላይ የደረሰውን የጥቃት ዛቻ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
የትራምፕ የሽግግር ቡድን ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት ተሿሚዎቹ ከነቤተሰቦቻቸው "አስፈሪ የጥቃት ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል" ብለዋል።
የጸጥታ አካላት ግን የእጩዎቹን ደህንነት ለማረጋገጥ በፍጥነት ተንቀሳቅሷል ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
ቃል አቀባዩዋ ሁለት የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ዳግም የተመረጡት ትራምፕ አይበገሬነት በማንሳት "ዛቻ እና አመጽ እንደማይገታን ትራምፕ ጥሩ ተምሳሌት ናቸው" ሲሉም ተናግረዋል።
ትራምፕ በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሆኑ የመረጧቸው የኒውዮርኳ ኤሊስ ስቴፋኒክ የጥቃት ዛቻ እንደደረሳቸው በመግለጽ የመጀመሪያዋ ሲሆኑ የእርሳቸውና የቤተሰቦቻቸው ቤት የቦምብ ጥቃት ኢላማ መሆኑ እንደተነገራቸው ተናግረው ነበር።
ስቴፋኒክ ከባለቤታቸው እና የሶስት አመት ልጃቸው ጋር ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ ኒውዮርክ እያሽከረከሩ ሲጓዙ ነው ማስፈራሪያው የደረሳቸው።
የመከላከያ ሚኒስትር እንዲሆኑ የታጩት ፔት ሄግሴትም የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፥ "የትኛውም ማስፈራሪያ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የጣሉብኝን አደራ ከመወጣት አያግደኝም" ብለዋል።
የ78 አመቱ አዛውንት ዶናልድ ትራምፕ በስልክ ጥሪ የተላለፈው የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ እንዳልደረሳቸው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉዳዩ ዙሪያ ገለጻ እንደተደረገላቸውና የደህንነት አካላት ከትራምፕ የሽግግር ቡድን ጋር በመቀናጀት ክትትል እያደረጉ መሆኑን ዋይትሃውስ አስታውቋል።