ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር የቀጥታ ውይይት ለማድረግ እየጣሩ እንደሚገኙ ተነገረ
የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች በወቅታዊ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ መሪዎች የሚመክሩበትን ሁኔታ እያመቻቹ ነው ተብሏል
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው በዲፕሎማሲ ስኬት ከሚነገርላቸው ውጤት መካከል ከሰሜን ኮርያ መሪ ጋር ያደረጉት ውይይት አንዱ ነው
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር በቀጥታ ለመወያየት ሙከራዎችን እያደረጉ እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡
በሰሜን ኮርያ ልሳነ ምድር እየተባባሰ የመጣው ውጥረት ወደ ግጭት እንዳያድግ ፕሬዝዳንቱ እያደረጉት በሚገኘው ጥረት አማካሪዎቻቸው ቀጥተኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መስመርን ለመዘርጋት እየጣሩ ስለመሆናቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ በሰሜን ኮርያ ጉዳይ ስለሚከተሉት ፖሊሲ ይፋዊ ማብራርያን እስካሁን ባይሰጡም በመጀሪያው የስልጣን ዘመናቸው እንደነበረው ከኪም ጆንግ ኡን ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየት ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡
ኪም ለትራምፕ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥያቄ ምን አይነት ምላሽ እንደሚሰጡ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም ባለፉት አራት አመታት የጆ ባይደን አስተዳደር ያቀረበውን የእንነጋገር ጥያቄዎች በሙሉ ውድቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
ከዚህ ባለፈም ፒዮንግያንግ በጆ ባይደን አስተዳደር ዘመን የረጅም ርቀት እንዲሁም የአህጉር አቋራጭ ሚሳይሎችን ሙከራ እና ምርት አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
በትራምፕ ዘመን የተሸሻለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መስርተው ከነበሩት ደቡብ ኮሪያም ጋር ያለው ውጥረት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ኪም ከደቡብ ኮርያ ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ከማፍረሳቸው በዘለለ በሁለቱ ጎረቤታሞች መካከል ያለው የፕሮፖጋንዳ ፍልሚያም ከፍ ብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፒዮንግያንግ እና ሞስኮ ወዳጅነታቸውን እያጠናከሩ ሲሆን የጋራ የደህንነት እና የመከላከያ አጋርነት ስምምነትም ፈጽመዋል፡፡
10 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በአሁኑ ወቅት ለሩስያ ተሰልፈው ዩክሬንን እየተዋጉ መሆናቸው ደግሞ አዲስ አለማቀፋዊ ትኩሳትን ያስከተለ ሁነት ሆኗል፡፡
ከ2017-2021 የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ትራምፕ በሲንጋፖር፣ ሃኖይ እና በኮሪያ ድንበር ላይ ከኪም ጋር ሶስት ስብሰባዎችን አድርገዋል፡፡
ሮይተርስ በሁለቱ መሪዎች መካከል አዲስ ግንኙነት ለመመስረት ጥረት ከሚያደርጉ የትራምፕ ሰዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት አዲሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ምን ውጤት እንደሚያስገኝ ግልጽ አይደለም ፡፡
የመጀመሪያው የትራምፕ አላማ መሰረታዊ ግንኙነትን እንደገና መመስረት ነው፤ ነገር ግን ለዚህ ተጨማሪ የፖሊሲ ማስፈጽሚያዎች እና ትክክለኛ የጊዜ ሰሌዳ አልተዘጋጀም ብለዋል፡፡
አማካሪዎቹ የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ በመካከለኛው ምስራቅ እና በዩክሬን ለሚገኙ አሳሳቢ የውጭ ፖሊሲ ስጋቶች ምላሽ ከተሰጠ በኋላ ሊከተል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡