ዶናልድ ትራምፕ ጾታቸውን የቀየሩ 15 ሺህ የአሜሪካ ጦር አባል ወታደሮችን ከስራ እንደሚያግዱ ተገለጸ
ጾታቸውን የቀየሩ ወታደሮች በቀጣይ የሀገሪቱን ጦር እንዳይቀላቀሉ እገዳ ይጥላሉም ተብሏል
የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የአሜሪካ ጦር አባላትን ቁጥር ሊያመናምነው እንደሚችል ተገልጿል
ዶናልድ ትራምፕ ጾታቸውን የቀየሩ 15 ሺህ የአሜሪካ ጦር አባል ወታደሮችን ከስራ እንደሚያግዱ ተገለጸ።
ከአንድ ወር በፊት 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎች ከወዲሁ ማነጋገራቸውን ቀጥለዋል።
ጥር አጋማሽ ላይ ስልጣን የሚይዙት ዶናልድ ትራምፕ ካቢኔያቸውን እያዋቀሩ ሲሆን የፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ፔቴ ሄግሴትን የመከላከያ ሚንስትር እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
ሰዎች ተፈጥሯዊ ጾታዎችን መቀየር የለባቸውም ብለው የሚያምኑት ዶናልድ ትራምፕ ጾታቸውን የቀየሩ እና የሀገሪቱ ጦር አባላት የሆኑ ወታደሮችን ከስራ እንደሚያግዱ ታየምስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ 15 ሺህ ጾታቸውን የቀየሩ ወታደሮችን የማባረር እቅድ አላቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ተፈጥሯዊ ጾታቸውን የቀየሩ አሜሪካዊያን የሀገሪቱን ጦር መቀላቀል እንዳይችሉ እገዳ እንደሚጥሉም ተገልጿል።
ዶኔልድ ትራምፕ በከ2016-2020 ድረስ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው ዓመታት ውስጥ ተፈጥሯዊ ጾታቸውን የቀየሩ ዜጎች የአሜሪካ ጦርን እንዳይቀላቀሉ እገዳ ጥለው የነበረ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህንን እገዳ አንስተውታል።
ይሁንና አንዳንድ ተንታኞች ግን የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የአሜሪካ ጦር የሰው ሀይል መመናመን እንዲገጥመው ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ጾታቸውን የቀየሩ የአሜሪካ ጦር አባላት ከስራ ከታገዱ አሜሪካ እነሱን ለመተካት እስከ 20 ዓመታት ሊወስድ ይችላል ማለታቸው ተገልጿል።