ትራምፕ በስልጣን ጊዜያቸው የመጀመርያ ቀን በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይና ላይ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ዛቱ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ የ25 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ አድርጋለሁ ብለዋል
ሀገራቱ አሜሪካን ከሚጎዳ ድርጊት እስካልተቆጠቡ ድረስ የታሪፍ ጭማሪው ከዚህ በላይም እንደሚያሻቅብ አስጠንቅቀዋል
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመርያ ቀን የኋይት ሀውስ ቆይታቸው በካናዳ ቻይና እና ሜክሲኮ ላይ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ዛቱ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጭማሪውን የሚያደርጉት ህግ ወጥ ስደትን እና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመቆጣጠር ነው ተብሏል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከጥር 20ው በአለ ሲመታቸው በኋላ ከሜክሲኮ እና ካናዳ በሚመጡ ዕቃዎች ላይ የ 25 በመቶ ታሪፍ የሚጥል ማስፈጸሚያ ትዕዛዝ ላይ እፈርማለው ብለዋል።
በሁለቱ ጎረቤቶች ላይ የሚጣለው የታሪፍ ጭማሪ መነሻቸውን ከሀገራቱ ያደረጉ አደንዛዥ እጾች እና ህገ ወጥ ስደተኞች እስከሚቆሙ ድረስ ተግባራዊነቱ እንደሚቀጥል ነው የተገለጸው፡፡
የአሜሪካ መንግስት “ሴንቴቲክ ኦፒዮይድ ፌንቴኔል” የተሰኘ አደንዛዥ እጽ ከካናዳ እና ቻይና በሰፊው ወደ አሜሪካ እየገባ እንደሚገኝ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የባይደን አስተዳደር ባለፈው ዓመት ወደ 75 ሺህ አሜሪካውያን ሞት መንስኤ ነው የተባለው “ፌንቴኔል” እጽ ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ንጥረ ነገሮችን ከማምረት እንድትቆጠብ ቤጂንግን አስጠንቅቆ ነበር፡፡
ትራምፕ “ትሩዝ” በተሰኝው ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ሜክሲኮ እና ካናዳ ችግሩን በቀላሉ ለመፍታት መፍትሄው በእጃቸው ነው ይህ የማይሆን ከሆነ ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በተጨማሪም በቻይና ላይ ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣል ማስታወቃቸውን ተከትሎ ከአሜሪካ ሶስት ታላላቅ የንግድ አጋሮች ጋር የምትገባበት ውጥረት ሊባባስ ይችላል ተብሏል፡፡
በዋሽንግተን የቻይና ኢምባሲ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጡት ማብራርያ “የቻይና አሜሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር በጋራ ጥቅም የተመሰረተ ነው፤ ማንም በንግድ ጦርነት ወይም በታሪፍ ጦርነት የሚያሸንፍ የለም” ብለዋል።
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ትራምፕ ሜክሲኮ እና ቻይና አሜሪካን ከሚጎዳ ድርጊታቸው ካልታቀቡ እስከ 100 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀው ነበር፡፡
ከዚህ ባለፈም ለቻይና ኩባንያዎች ብቻ የተመቸ ነው ያሉትን የንግድ ስርአት በተለያዩ መንገዶች እንደሚያስተካክሉም ቃል ገብተዋል፡፡
ታሪፍ የትራምፕ የኢኮኖሚ ራዕይ ዋና ማዕከል ነው። ተመራጩ ፕሬዝዳንት የአሜሪካን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የአሜሪካን ኩባንያዎች ለመጠበቅ እና የታክስ ገቢን ለማሳደግ እንደ ዋነኛ መንገድ ይመለከቱታል፡፡