ሩሲያዊው “የሞት ነጋዴ” የአክራሪ ብሔርተኞች ስብስብ ወደ ሆነው ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተቀላቀለ
ቡት የተቀላቀለበት ፓርቲ ማኒፌስቶ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሀገሮችን እንደገና ወደ አንድ ማምጣት የሚል ነው
የፓርቲው መሪ፤ ደፋሩ ቪክተር ቡት በፓርቲው ውስጥ ተገቢ ቦታ ይኖሯል ብለዋል
አሜሪካ ከእስር የለቀቀቸው ሩሲያዊው “የሞት ነጋዴ” ቪክተር ቡት የአክራሪ ብሔርተኞች ስብስብ ፓርቲ ወደሆነው የሩሲያውን ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ተቀላቀለ፡፡
ቪክተር ቡት የተቀላቀለው ፓርቲ ክሬምሊንን በመደገፍ የሚታውቅ ነው፡፡
የፓርቲው መሪ ሊዮኒድ ስሉትስኪ “ እርግጠኛ ነኝ ደፋሩ ቪክቶር ቡት በፓርቲው ውስጥ ተገቢ ቦታ ይወስዳል” ማለታቸውም ሮይተረስ ዘግቧል፡፡
እንደፈረንጆቹ በ1991 የተመሰረተው የሩሲያው ሊበራል ዴምክራቲክ ፓርቲ ጽንፈኛ ብሔራዊ ርዕዮተ ዓለም በማራመድ ይታወቃል።
የፓርቲው ማኒፌስቶም የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሀገሮችን እንደገና ወደ አንድ ማምጣት የሚል ነው፡፡
በዚህም በአሁኑ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የክሬምሊን ባለስልጣናትን በመደገፍ ትልቁን ድርሻ በመወጣት ላይ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ ይገለጻል፡፡
ሩሲያ በእስር ላይ ለነበረችው ዝነኛዋ አሜሪካዊት የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግራይነር ልዋጭ ቡት ይፈታልኝ ማለቷን ተክትሎ ቪክተር ቡት ከቀናት በፊት ከአሜሪካ እስር ቤት ሊፈታ እንደቻለ የሚታወስ ነው፡፡
የእስረኞች ልውውጡ የተሳለጠው በሳኡዲው ልዑልና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቱ አቻቸው አማካኝነት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
“የሞት ነጋዴ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ቡት የሩሲያ ዜግነት ያለው ሲሆን እጅግ አደገኛ የተባለ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ነጋዴና አዘዋዋሪ ነው።
የ55 አመቱ አዛውንት በአንዳንድ የምድራችን ደም አፋሳሽ ግጭቶች አማጺዎችን በማስታጠቅ ይከሰሳል።
ሆሊውድ በርሱ ህይወት ላይ ‘ሎርድ ኦፍ ዎር’ የተሰኘ ፊልም እስከመስራት ደርሷል።
25 ዓመታት ጽኑ እስር ተፈርዶበት የነበረው ቪክቶር ቡት ላለፉት 12 ዓመታት በአሜሪካ እስር ቤት ነበር።