ኔቶ ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት ሊያስገቡ ከሚችሉ ድርጊቶች እየተጠነቀቀ መሆኑን አስታውቋል
ሩሲያ እና ኔቶ ወደ ይፋዊ ጦርነት ሊያመሩ እንደሚችሉ ተገለጸ።
ለጥቂት ሳምንታት ብቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት 10 ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ይህ ጦርነት ምክንያት የጦርነቱ ቀጥታ ተሳታፊ የሆኑት የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ከመጉዳቱ ባለፈ የዓለም ምግብ፣ ነዳጅ እና ዲፕሎማሲን አናግቷል።
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ዩክሬንን በመደገፍ ቀዳሚው ተቋም ሲሆን ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት እንድታሸንፍ የጦር መሳሪያ፣ ወታደራዊ መረጃዎች፣ ወታደሮችን ማሰልጠንን ጨምሮ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎችን እየሰጠ ይገኛል።
የኔቶ ዋና ጸሀፊ ጄንስ ስቶልትንበርግ እንዳሉት "ሩሲያ እና ኔቶ ወደ ይፋዊ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ" ሲሉ መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ኔቶ ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት እንዳይገባ በየዕለቱ በርካታ ጥንቃቄዎችን እያደረግን ነው የሚሉት ዋና ጸሀፊው የሆነ ስህተት ከተፈጠረ የአውሮፓ ሀገራትን ያሳተፈ ጦርነት ሊጀመር ይችላል ሲሉም አክለዋል።
ሁለቱ አካላት ወደ ጦርነት ከገቡ በታሪክ አስከፊው ጦርነት በአውሮፓ ምድር ይካሄዳልም ብለዋል የኔቶ ዋና ጸሀፊ ጄንስ ስቶልትንበርግ።
ሩሲያ በበኩሏ የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ከመስጠት እንዲቆጠቡ አሳስባለች ።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጥቃትን በመስጋት አስቀድመን ኑክሌር አንተኩስም ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የጥቃት ሙከራ ከተፈጸመብን ግን በሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤሎቻችን እናጠቃለን፣ ይህ ቀልድ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።