ለ“ታገቢኛለሽ? ጥያቄ“ በፍቅረኛዋ የተጠለፈችው እንስት ፍቅረኛዋን እና ተባባሪዎቹን ከሰሰች
ፍቅረኛዋ የታገቢኛለሽ? ጥያቄውኝ ለየት ባለ መንገድ ለመፈጸም በሚል ድርጊቱን እንዳደረገው ገልጿል
የተጠለፈቸው እንስት በበኩሏ "ድርጊቱ ፍጹም አስፈሪ ነበር፤ ስሜቴን ጎድቶታል፤ ፍትህ ያስፈልገኛል" ብላለች
ለ“ታገቢኛለሽ? ጥያቄ“ በፍቅረኛዋ የተጠለፈችው እንስት ፍቅረኛዋን እና ተባባሪዎቹን ከሰሰች፡፡
በብሪታንያ አንድ ወጣት ከሁለት ዓመት በላይ በፍቅር ከቆዩት ፍቅረኛው ጋር በጋብቻ ሊተሳሰር ይወስናል፡፡
በዚህ ውሳኔው ይነሳሳ እና ለቅርብ ጓደኞቹ ጉዳዩን ያስረዳቸዋል፡፡ ጓደኞቹም በጓደኛቸው ውሳኔ ይደሰቱና እቅዱ ስለሚሳካበት መንገድ ይወያያሉ፡፡
በመጀመሪያ ግን የታገቢኛለሽ? ጥያቄ ለፍቅረኛው ማቅረብ እንዳለበት የተስማሙት ጓደኛሞች ይህ እቅድ ለየት ባለ መንገድ እንዲሰናዳ ይወስናሉ፡፡
ከብዙ እቅዶች መካከልም ይህ ሊያገባ የወሰነው ወንድ ፍቅረኛውን የተጠለፈች እንዲመስላት በመጨረሻም ከጠበቀችው በተቃራኒ የታገቢኛለሽ? ጥያቄ ማቅረብ የሚለው ይጸድቃል፡፡
ለዚህ እቅድ መሳካትም ዝግጅት ተጀምሮ ፍቅረኛ የተባለችውን እንስት በመጥለፍ ዝግጅቱ ወደተሰናዳበት ስፍራ የሚያመጡ ጠላፊዎች፣ ተሽከርካሪ እና ሌሎችም ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡
የታገቢኛለሽ? ጥያቄ አቅራቢው ወጣት ፍቅረኛዋ ከሰሞኑ ለስራ ከከተማ ዘወር እንደሚል የተነገራት እንስት በጠዋቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሩጫ ላይ እያለች በማታውቃቸው ሰዎች ትታገታለች፡፡
በፊት መሸፈኛ ጭምብል ወይም ማስክ በተሸፈኑ ሰዎች በሀይል ተያዛ ወደ አንድ ተሸከርካሪ ከዚያም አይኗን ተሸፍና ወደተዘጋጀላት ስፍራ የተወሰደችው ይህች ፍቅረኛ በድንጋጤ እና ፍርሃት ውስጥ ሆና ወደማታውቀው ስፍራ ትወሰዳለች፡፡
በመጨረሻም ከተሳፈረችበት ተሸከርካሪ እንድትወርድ ከተደረገች በኋላ አይኗ ሲገለጥ ፍቅረኛዋ ተንበርክኮ ቀለበት ይዞ ታገኘዋለች፡፡
ይሁንና በእቅዳቸው ትደሰታለች የተባለችው ፍቅረኛ በእንባ ትሞላለች፡፡ በዚህ የተደናገጠው ፍቅረኛዋ ጓደኞቹን እንዲሄዱ ካደረገ በኋላ ወደ እሷ ሊቀርባት ይሞክራል፡፡
በተፈጸመባት ነገር የተበሳጨችው ይህች እንስት ጉዳዩን ወደ ህግ እንደወሰደችው ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
በቦይፍሬንዷ የተጠለፈችው ይህች እንስት ጉዳዩን ለፖሊስ ስታስረዳ በድንጋጤ ልብሷ ላይ መጸዳዳቷን፣ ድንጋጤ ፍርሃት እና ሌሎች ጉዳቶች እንደደረሱባት ተናግራለች፡፡
ፍቅረኛዋ እና ጓደኞቹ ይቅርታ እንደጠየቋት የምትናገረው ይህች እንስት ይቅርታ ማድረግ እንደከበዳት እና ክሱን እንደምትቀጥልበት የተናገረች ሲሆን ፖሊሶች ድርጊቱ ሲፈጸምባት የተቀረጸ ተጨማሪ ቪዲዮ እንድትሰጣቸው እየወተወቷት መሆኑን አክላለች፡፡