በቢሮ ውስጥ የሚጀምር ድብቅ የፍቅር ግንኙነትን እንዴት በቀላሉ ማወቅ ይቻላል?
ጥንዶች በስራ ቦታ የፍቅር ግንኙነት ሲጀምሩ አብዛኛውን ነገር ለመደበቅ ቢሞክሩም በአንድ ነገር ግን ግንኙነታቸው ይገለጣል፤ በሳቃቸው
በአሜሪካ ባልቲሞር ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት በቢሮ ውስጥ የጥንዶችን አሳሳቅ በማየት ብቻ የፍቅር ግንኙነት ስለመጀመራቸው ማወቅ እንደሚቻል አሳይቷል
የስራ ባልደረቦች በቢሮ ውስጥ የፍቅር ግንኙነት ሲጀምሩ ሚስጢራዊ እንዲሆን የማያደርጉት ጥረት የለም።
ለምሳ አብረው ከመውጣት እና አብረው መታየትንም ይሸሻሉ፤ አሳሳቃቸውና አወራራቸውም የተመጠነ ይሆናል።
ከስራ ባልደረባነትና ጓደኝነት የዘለለው ሚስጢራዊ የፍቅር ግንኙነት ስለመጀመራቸው ለማወቅም አዳጋች ሲሆን ይስተዋላል።
በአሜሪካ ባልቲሞር ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ግን በአንድ ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ከጓደኝነት የተሻገረ ግንኙነት ያላቸውን ጥንዶች በአንድ ወይንም በሁለት ሰከንድ ማወቅ እንደሚቻል አመላክቷል።
እንዴት እንደሚስቁ በማየት ብቻ ድብቅ የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸውን ማወቅ ይቻላል ይላል ጥናቱ።
በቢሮ ውስጥ ፍቅር የጀመሩ ጥንዶች ሲስቁ ደግሞ “ድምጻቸው የመቅጠን፣ እንደ ልጅ የመሆን” ባህሪ ይታይባቸዋል፤ ብዙ ጊዜም ሀፍረት ከፊታቸው ላይ ይነበባል።
በተቃራኒው የፍቅር ግንኙነት የሌላቸው የስራ ባልደረቦች ሲስቁ ያለምንም ጭንቀት ጮክ ብለው ነው፤ ሳቃቸው ውስጥም መዝናናት ይታያል ይላሉ የጥናቱ ዋና ጸሃፊ ፕሮፌሰር ሳሊ ፋርሊ።
በጥናቱ የስራ ቦታ የፍቅር ግንኙነት የጀመሩ እና ከባልደረባነትና ጓደኝነት የዘለለ ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ሲስቁ ድምጾች ተቀርጸው ሌሎች ሰዎች ሰምተው የትኞቹ ፍቅር እንደጀመሩ እንዲለዩ ተደርጓል።
የጥናቱ ተሳታፊዎችም ሳቃቸውን በመስማት ብቻ በቢሮ ውስጥ የፍቅር ግንኙነት የጀመሩትን ያለምንም ስህተት ለይተዋቸዋል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሳሊ።
የተቀዱትን የሳቅ ድምጾች ብቻ ሰምተው ከጓደኛ አልያም የስራ ባልደረባነት ያልዘለለውን ሚስጢራዊ የቢሮ ፍቅር ከጀመሩት እንዲለዩ የተደረጉት የህንድ፣ ሜክሲኮ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል እና አሜሪካ ዜጎች ናቸው።
ይህም ሳቅ አለማቀፋዊ ቋንቋነቱንና የሰዎችን የስሜት ለውጥ ለማወቅ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን ያመላክታል ብሏል የባልቲሞር ዩኒቨርሲቲ ጥናት።