በቀድሞ ፍቅረኞቹ ሰላማዊ ሰልፍ የተደረገበት ሙሽራም በድርጊቱ ማፈሩን ገልጿል
በደቡባዊ ቻይና ዩናን ግዛት ነዋሪ የሆነው ቼን ከሚወዳት ፍቅረኛው ጋር ትዳር ለመመስረት ቀነ ቆርጠው ለረጅም ጊዜ ማቀዱን ይናገራል፡፡
ያሳለፍነው የካቲት 6 ቀን ደግሞ የቼን እና ፍቅረኛው ጋብቻ የሚመሰርቱባት ዕለት ነበረች፡፡ ሁሉም ነገር በሰላም እየተካሄደ እያለ ግን መፈክር ያነገቡ የቼን የቀድሞ ፍቅረኞች ጋብቻው ወደ ሚፈጸምበት ስፍራ ይደርሳሉ፡፡
የቼን የቀድሞ ፍቅረኞችም የሙሽራውን ጉድ እናወጣለን የሚል መፈክራቸውን አንግበው ከሰርጉ ቦታ መታየታቸው ሰርጉን ለመታደም በስፍራው የነበሩ አጃቢዎችን እና ሌሎች ሰዎችን ትኩረት ስበዋል፡፡
ብዙዎችም ሙሽራው ምን አድርጓችሁ ነው እምትፈልጉትስ ምንድን ነው በሚሉ ጥያቄዎች ሲጠየቁ ዛሬ ጋብቻውን የሚፈጽመው ቼን ከዚህ በፊት ፍቅረኛችን ነበር አታላይ እና ዉሸታም ነው በድሎናል ሲሉ መናገራቸውን የብሪታንያው ሚረር የቻይና ብዙሃን መገናኛዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
በቀድሞ ፍቅረኞቹ ድርጊት የተደናገጠው ሙሽራው በስራው ማፈሩን፣ የእንስቶቹ ድርጊትም ትክክል መሆኑን ተናግሯል ተብሏል፡፡
ድርጊቱን በወጣትነቱ የዕድሜ ወቅት እንዳደረገው የተናገረው ሙሽራው ከዚህ በፊት አስተሳሰቤ ትክክል አልነበረም አሁን ግን ተለውጫለሁ ሲል እንደተናገረም ተገልጿል፡፡
የቀድሞ ፍቅረኞቹ ድርጊት በቻይና ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ለበርካታ ቀናት ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ የቆየ ሲሆን ሙሽራዋ ይህን ጋብቻ ስለ ማፍረሷ አልያም ስለመቀበሏ ግን የተባለ ነገር የለም፡፡
በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎችም በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ሀሳቦችን በብዛት እንደጻፉ ሲገለጽ ሙሽራው ከብዙ ሴቶች ጋር ፍቅር መመስረቱን እንደ ጥፋት ቆጥረው ሲጽፉ ገሚሶቹ ደግሞ ችግሩ ሴቶቹን መበደሉ እና ይቅርታ አለመጠየቁ እንጂ ከብዙ ሴቶች ጋር ፍቅር መመስረቱ አይደለም ሲሉ ጽፈዋል