አዲሱ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ቃለ መሃላ ፈጸሙ
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ለኮቪድ-19 ቫይረስ ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠታቸው “ዘር ማጥፋት” ፈጽመዋል ሲሉ ከሰዋል
ሽንፈቱን ለመቀበል አሻፈረኝ ሲሉ የከረሙት ቦልሴናሮ አርብ እለት ብራዚልን ለቀው አሜሪካ ገብተዋል
ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ እሁድ እለት የብራዚል ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት በቀድሞው መሪ ጃየር ቦልሶናሮ ላይ ከባድ ክስ በማቅረብ በረሀብ ፣ በድህነት እና በዘረኝነት የተመሰቃቀለውን ህዝብ ለመታደግ ከባድ ለውጥ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ።
ሉላ የላቲን አሜሪካዋን ትልቅ ሀገር ለመምራት በይፋ ስልጣን ከያዙ በኋላ ለም/ቤቱ ባደረጉት ንግግር፤ የጥቅምቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እውነተኛ አሸናፊ ዲሞክራሲ ነው ብለዋል ።
ሽንፈቱን ለመቀበል አሻፈረኝ ሲሉ የከረሙት ቦልሴናሮ አርብ እለት ብራዚልን ለቀው አሜሪካ ገብተዋል።
ሉላ ቦልሶናሮን በስም ሳይጠቅሱ “ሀገሪቷን ለግል እና ርዕዮተ-ዓለማዊ ጥቅም ለመግዛት በሞከሩት ላይ ምንም አይነት የበቀል መንፈስ አንይዝም፤ ነገር ግን የህግ የበላይነትን እናረጋግጣለን” ብለዋል። "እነዚያ የተሳሳቱ ሰዎች ለኃጢአታቸው መልስ ይሰጣሉ" ሲሉም አክለዋል።
በተጨማሪም ከ680 ሽህ በላይ ብራዚላውያንን ለገደለው የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠት የቦልሶናሮ አስተዳደር “ዘር ማጥፋት” ፈጽሟል ሲሉ ከሰዋል።
"ለዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ኃላፊነቱ ይጣራል። ከቅጣት ነጻ መሆን አይቻልም" ብለዋል።
ምንም እንኳን የቦልሶናሮ የፍሎሪዳ ጉዞ በብራዚል ውስጥ ካሉ ከማንኛውም የህግ አደጋዎች የሚከላከል ቢሆንም፤ ከጸረ-ዲሞክራሲያዊ ንግግራቸው እና ከወረርሽኙ አያያዝ ጋር በተያያዘ የፕሬዝዳንትነት ያለመከሰስ መብታቸውን ካጡ በኋላ የመከሰስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተብሏል።
የሉላ የመንግስት እቅድ ከቦልሶናሮ የአራት ዓመታት የስልጣን ዘመን ጋር ፍጹም ይለያል መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሉላ ከዓለም ከፍተኛ የምግብ አምራቾች መካከል አንዷ የሆነችውን ብራዚልን ወደ አረንጓዴ ልዕለ ኃያልነት መለወጥ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።