የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየር የሳኡዲን ሊግ ለመቀላቀል አንድ ቢሊየን ዶላር ክፍያ ቀረበለት
ተጫዋቹ የ2034 የአለም ዋንጫ አዘጋጇ ሀገር አምባሳደር እንዲሆንም ተጠይቋል
ተጫዋቹ ሊጉን የሚቀላቀል ከሆነ ሳኡዲ ከአውሮፓ የምታስፈርመው የመጀመርያው ወጣት ተጫዋች ይሆናል፡
ብራዚላዊው የእግርኳስ ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየር የሳኡዲን ሊግ ለመቀላቀል ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ክፍያ ቀረበለት፡፡
በአሁኑ ወቅት በሪያል ማድሪድ ቤት በአጥቂ ስፍራ ላይ የሚጫወተው የ24 አመቱ ቪኒሲየስ በሳኡዲ ፐብሊክ ኢንቨስትመንት ፈንድ ሊጉን እንዲቀላቀል ጥሪ ቀርቦለታል፡፡
ተጫዋቹ በሊጉ ለሚኖረው የአምስት አመት ቆይታ በየአመቱ 218 ሚሊየን ዶላር እና የጉርሻ ክፍያ እንደሚከፈለው ቃል የተገባለት ሲሆን በተጨማሪም የ2034ቱ የአለም ዋንጫ አዘጋጅ የሆነችው ሳኡዲ አረብያ ለቀጣዮቹ አስር አመታት አምባሳደር እንዲሆን ታጭቷል፡፡
በቀረበለት ጥያቄ ላይ የተጨዋቹ ተወካዮች በሰጡት ምላሽ ይህን መሰል ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያዎች በጥሞና ጥናት የሚያስፈልጋቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ሆኖም ተጫዋቹ የቀረበለትን ጥያቄ በይፋ እንደማይቀበለው አላሳወቁም፡፡
ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለኢኤስፒኤን እንደተናገሩት ማድሪዶች ተጫዋቹን የመልቀቅ ፍላጎት ስለሌላቸው በዝውውር ጥያቄው ላይ ለመነጋገር ፍቃደኛ አይደሉም፡፡
በእግርኳሱ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ላይ የሚገኝው የሳኡዲ አረብያ ንጉሳዊ አስተዳደር ፐብሊክ ኢንቨስመንት ፈንድ የተባለው ድርጅት የሀገሪቱን አራት ዋና ዋና ክለቦች በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡
አልሀሊ ፣ አል ኢትሀድ ፣ አል ሂላል እና አል ናስር ድርጅቱ የሚያስተዳድራቸው ክለቦች ናቸው፡፡
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፣ ኔይማር ፣ ካሪም ቤንዜማ ፣ ሳዲዮ ማኒ እና ሌሎችንም የአውሮፓ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ማስፈረም የቻለው የሳኡዲ ሊግ ለፈረንሳዩ አጥቂ ኪሊያን ምባፔን ለማስፈርም ያቀረበው ጥያቄ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
አሁን ላይ ቪኒሲየስ ጁኒየር የቀረበለት የፊርማ ጥያቄም ለምባፔ ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
እስከ 2027 ድረስ ከማድሪድ ጋር የሚያቆይ ስምምነት ያለው የ24 አመቱ ብራዚላዊ ኮከብ ቪኒሲየስ ከብራዚሉ ክለብ ፍላሚንጎ ሎስብላንኮዎችን የተቀላቀለው በ2018 ነው፡፡
ቪኒሲየስ ባለፈው የውድድር አመት ባደረጋቸው 39 ጨዋታዎች 24 ጎሎችን አስቆጥሮ 11 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል የተሳካ የውድድር አመት አሳልፏል፡፡
በቆይታውም ሁለት የሻምፒውንስ ሊግ እና 3 የላሊጋ ዋንጫዎችን በቡድኑ ማንሳት ችሏል፡፡
በሪያል ማድሪድ ቤት ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ተጫዋቹ በተደጋጋሚ በሚደርስባት የዘረኝነት ጥቃት መነጋገርያ መሆኑ ይታወቃል፡፡