ብሪክስ ለዓለም ንግድ ከዶላር ውጪ ተጨማሪ መገበያያ ገንዘብ መፍጠር ላይ እንደሚያተኩር ገለጸ
ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን እና አረብ ኢምሬት ብሪክስን በቅርቡ ሊቀላቀሉ ይችላሉ ተብሏል
የብሪክስ አባል ሀገራት በደቡብ አፍሪካ ኬፕታወን መክረዋል
ብሪክስ ለዓለም ንግድ ከዶላር ውጪ ተጨማሪ መገበያያ ገንዘብ መፍጠር ላይ እንደሚያተኩር ገለጸ፡፡
በብራዚል፣ ሕንድ፣ ሩሲያ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ህብረት የተመሰረተው እና በምህጻረ ቃሉ ብሪክስ በመባል የሚጠራው ስብስብ የምዕራባዊያንን ተጽዕኖ ለመመከት በሚል ነበር በፈረንጆቹ 2009 ላይ የተቋቋመው፡፡
ዋና መቀመጫውን ቻይና ያደረገው ይህ የአምስት ሀገራት ስብስብ ከዓለም ህዝብ ብዛት ውስጥ 42 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ከሚመራው ቡድን ሰባት ሀገራት ስብስብ ጋር ሲነጻጸር በዓመታዊ ገቢም ሆነ በህዝብ ብዛት ይበልጣል፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በደቡብ አፍሪካ ኬፕታወን ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን ለዓለም ንግድ ዋነኛ መገበያያ የሆነው ዶላር ተጨማሪ መገበያያ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ እና ዓለም በጥቂት ሀገራት የበላይነት መመራቷ ማብቃት አለበት የሚለው ዋነኛ የመወያያ ጉዳዮች ነበሩ ሲል ዶቸ ቪሌ ዘግቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የብሪክስ አባል ሀገራትን ስብስብ ለመቀላቀል በይፋ ያመለከቱ ሀገራትን መቀበል የሚለው ሌላኛው መወያያ አጀንዳ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የነዳጅ ሀብታሟ ሀገር ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት የብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን ያቀረቡ ሲሆን ስብስቡ ለነዚህ ሀገራት ፈቃድ በቅርቡ እንደሚሰጥ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የሕንዱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራማንያም ጄሻንካር በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው ላይ "ዓለም በጥቂቶች ሳይሆን በብዙዎች እየተመራች ነው፣ የቆዩ ችግሮቻችንን መፍታት የምንችለው በአዳዲስ አስተሳሰቦች ነው፣ እኛ የአዲስ ለውጥ ምልክቶች ነን" ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም የኢኮኖሚ የበላይነቱ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ መወሰኑ ብዙ ሀገራትን በጥቂቶች ጫና ስር እንዲወድቁ ማድረጉንም በጉባእው ላይ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ናለዲ ፓንደር በበኩላቸው አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት አለመወከሏን ተችተዋል፡፡
የብሪክስ ዓመታዊ ጉባኤ የፊታችን ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ የሚጠበቅ ሲሆን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡